የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ሰለሞን ባረጋ በሻንጋይ ዳይመንድ ሊግ አሸነፈ
በሴቶች የ5 ሺህ ሜትር ውድድርም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 4ኛ ተከታትለው ገብተዋል
የ2024 ዋንዳ ዳይመንድ ሊግ ውድድር ለ6 ወራት የሚቆይ ሲሆን በአራት አህጉራት በ15 ከተሞች ይካሄዳል
በሻንጋይ ዳይመንድ ሊግ የ5 ሺህ ሜትር ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ጾታ አሸንፈዋል።
በወንዶቹ ውድድር የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ሰለሞን ባረጋ ወደ ድል ተመልሷል።
አትሌት ሰለሞን ባረጋ ውድድሩን ለማጠናቀቅ 12 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ የፈጀበት ሲሆን፥ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ ቢንያም መሃሪ ተከትሎት ገብቷል።
በሴቶቹ ተመሳሳይ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያለውን ደረጃ ይዘው አጠናቀዋል።
መቅደስ ዓለምሸት በ14 ደቂቃ ከ36 ሰከንድ በመግባት ባሸነፈችበት ውድድር፥ አያል ዳኛቸው፣ ለተሰንበት ግደይ እና ውብርስት አስቻለ ከ2ኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል።
በቅርቡ በቻይና ዢያሜን በተካሄደ የ2024 ዋንዳ ዳይመንድ ሊግ ውድድር አትሌት ጉዳፍ ጸጋይ እና አትሌት ለሜቻ ግርማ በ5 ሺህ ሜትር ውድድር ማሸነፋቸው ይታወሳል።
የ2024 ዋንዳ ዳይመንድ ሊግ ውድድር ለ6 ወራት የሚቆይ ሲሆን፤ በአራት አህጉራት በ15 ከተሞች የሚካሄድ ይሆናል።
ዳይመንድ ሊግ ከ2010 ጀምሮ ጎልደን ሊግ የተሰኘውን ውድድር ተክቶ በመካሄድ ላይ መሆኑ ይታወቃል።
የውድድሩ አሸናፊዎች በተለያዩ ከተሞች በሚያስመዘግቡት ውጤት ዳጎስ ያለ ሽልማት ይበረከትላቸዋል።