አገሪቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀችው በከፍተኛ ድርቅ መጠቃቷን ተከትሎ ነው
ሶማሊያ በከፍተኛ ድርቅ መጠቃቷን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀች፡፡
እየተባባሰ በመጣው ወቅታዊ የድርቅ ሁኔታ ላይ የሃገሪቱን ካቢኔ ለአስቸኳይ ስብሰባ የጠሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መሃመድ ሮብል አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አውጀዋል፡፡
“ሃገራችን በድንገተኛ ሰብዓዊ አደጋ ላይ ትገኛለች” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያጋጠመውን አስከፊ ድርቅ ሰላባዎች እንዲያግዙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ባለችው ጎረቤት አገር ሶማሊያ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ለከፋ ድርቅ ተጋልጠዋል፡፡
የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ፋርማጆ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ሮብል “የዘገየውን ምርጫ” ለማካሄድ ተስማሙ
በርካቶች ለችግር መዳረጋቸውን የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ማስተባበሪያ አስታውቋል፡፡
በሶማሊያ ባለፉት ሶስት የዝናብ ወቅቶች ዝናብ ያልዘነበ ሲሆን በተለይም ጁባ እና ሸበሌ ወንዞች የውሃ መጠናቸው በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሱ የድርቁን ደረጃ እንዳባባሰው ድርጅቱ አክሏል፡፡
የድርቅ መጠኑ በተለይም ከቀጣዩ ታህሳስ ወር ጀምሮ እስከ መጋቢት ድረስ እንደሚባባስ የገለጸው ድርጅቱ ተጎጂዎችን ለመርዳት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ መሆኑንም ጠቅሷል፡፡
1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዜጎቿ በድርቅ የተጋለጡባት ኬንያ የአደጋ ጊዜ አዋጅ አወጀች
የምስራቅ አፍሪካ በይነ መንግስታት ሰሞኑን ባወጣው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሪፖርት በኢትዮጵያ፣ሶማሊያ እና ኬንያ ባጋጠመ የዝናብ እጥረት ምክንያት 26 ሚሊዮን ዜጎች ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ከድርቁ በተጨማሪም የአየር ንብረት መዛባት፣ኮሮና ቫይረስ እና ግጭቶች እርዳታ የሚፈልጉ ዜጎችን ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሳድገው እንደሚችልም ተገልጿል፡፡