ሰሞነ ህማማት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህ ቤተ-ክርስቲያንና በምዕመኖች በልዩ ስርዓቶች ይታሰባል
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን የዐብይ ጾም ስምንተኛ ሳምንት ወይም የመጨረሻ ሳምንት ሰሞነ ህማማት (የህማማት ሳምንት) በመባል ይጠራል። ሰሞነ ህማማትን ቤተ-ክርስቲያኒቱና ምዕመናኑ በተለየ ስርዓት ይከናወናል።
በተለይም ከዐብይ ጾም ሌሎች ሳምንታት በተለየ ስርዓትና ክዋኔ ይታሰባል። ለዚህም ምክንያቱ ህማማት "የፈጣሪን ህመም" ታሳቢ በማድረክ ልዩ ህግና ስርዓት እንዳለው አባቶች ይናገራሉ።
ከሆሳዕና በዓል (እሁድ) ስድስት ሰዓት እስከ አርብ (ስቅለት) ማታ ድረስ ያሉት ቀናት ሰሞነ ህማማት ናቸው። የህማማት ቀናት አምስት ቀናት ከግማሽ መሆናቸውን የሚያብራሩት የመላከ ገነት ጽጌ ቅ/ጊዮርጊስ ቤተ-ክርስቲያን አስተዳዳሪ መላከ ገነት ክብሩ ገ/ጻድቅ፤ ሳምንቱ "ዘመነ ፍዳ" የሚታሰብበት ጊዜ መሆኑን ይናገራሉ።
በመሆኑም በ"ዘመነ አዲስ" የሚካሄዱና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ወትሮ የምታከናውናቸው ስርዓቶች በህማማት ቀናት አይከናወኑም። ህዝበ ክርስቲያኑ በሰሞነ ህማማት የፈጣሪውን መከራ በማሰብ በተለየ ስርዓት ሳምንቱን ይከውናል።
የትኞቹ የቤተ-ክርስያኒቱ የዘወትር ስርዓቶች አይተገበሩም? ምን አይነት አዲስ ስርዓቶችስ አሉ?
በሰሞነ ህማማት በቤተ-ክርስቲያን "ግብረ ህማማት" የሚባል መጽሀፍ እንደሚነበብና ለሳምንቱ የተዘጋጀ ልዩ ጸሎት እንደሚደረግ መላከ ገነት ክብሩ ተናግረዋል። ሆናኖም የሌሎች ስርዓቶች ክዋኔ ይገታል።
በቤተ-ክርስቲያን በሰሞነ ህማማት የማይከናወኑ ስርዓቶች፡-
ቅዳሴ አይቀደስም (ከጸሎተ ሀሙስ ውጭ)
ማህሌት አይቆምም
ጸሎተ ፍትሀት አይደረግም
መስቀል አይሳለምም
ክርስትና አይነሳም
ኑዛዜ አይሰጥም አይቀበልም
እነዚህ ስርዓቶች በሆሳዕና ዕለት አስቀድመው የሚከናዎኑ መሆናቸውን መላከ ገነት ለአል ዐይን ተናግረዋል።
ምዕመናንስ ሰሞነ ህማማትን በምን ስርዓት ይከውናሉ?
በቤተ-ክርስቲያኗ "የመከራ ዘመን" የሚባለውን 5500 ዓመትን በመወከል አምስት ቀናት ተኩል የሆነው ሰሞነው ህማማት በምመናን ዘንድ በተለያዩ ድርጊቶች ይታሰባልም፡፡ የሚተገበሩ ድርጊቶች ሀዘንን ለመግለጽ እንዲሁም ከአስተምሮ ጋር መልዕክ ያላቸው መሆናቸውን መላከ ገነት ገብሩ ይገልጻሉ፡፡
መጨባበጥና መሳሳም የለም
ባዶ እግር -kôm
ስግደት
ጸሎት
ራስን ዝቅ ማድረግ ይታሰባል።
መላከ ገነት ክብሩ ገ/ጻድቅ በህማማት ሳምንት ምዕመኑ ወደ ራሱ ጠልቆ በመግባት እንዲጸልይ ጠይቀዋል።
"ሰው ስለ ኃጢያቱ ነው ማሰብ ያለበት፤ ስለ ሀገሩ ነው ማዘን ያለበት፤ ለሰላም ነው መጸለይ ያለበት፤ የሰው ልጅ ሰላም እንዲያገኝ፣ ሰላም ያጣው ህዝብ ሰላም እንዲያገኝ፤ እሱ [ፈጣሪ] የተቀበለውን መከራ በማሰብ ለሀገር ሰላም ስጥ፣ ህይወታችንን አስካክልልን፣ ከኃጢያታችን ይቅር ይበለን በማለት ይጸልዩ" ብለዋል።