የፋሲካ በዓልን በማስመልከት በዩክሬን የተኩስ አቁም እንዲደረግ ተመድ ጠየቀ
የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኑዮ ጉቴሬዝ የ4 ቀና የተኩስ አቁም ጥሪ አቅርበዋል
በዩክሬን የተጠየቀው የተኩስ አቁሙ ከነገ ፀሎተ ሀሙስ እስከ እሁድ የፋሲካ እለት ድረስ የሚቆይ ነው
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የትንሳዔ (ፋሲካ) በዓልን በማስመልከት በዩክሬን የተኩስ አቁም እንዲደረግ ጥሪ አቀረቡ።
ጉቴሬዝ ባቀረቡት ጥሪ “በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ዘንድ በሚከበረው በዚህ ቅዱስ ሳምንት ለተጎጂዎች እርዳታ እንዲደርስ እና ነጹሃንን ከጦርነት ቀጠና ለማስወጣት የአራት ቀናት የተኩስ አቁም ይደረግ” ብለዋል።
ጉቴሬስ በዩክሬን ያለውን አስከፊ ሁኔታ ሲገልጹም፤ “የሰብአዊ ፍላጎቶች ማሟላት በጣም አሳሳቢ ሆነዋል፤ ሰዎች የታመሙትን ወይም የቆሰሉትን ለማከም እንዲሁም የዕለት ተዕለት ኑሮ ለመኖር ምግብ፣ ውሃ እና ሌሎች አስፈላጊ አቅርቦቶች የላቸውም” ብለዋል።
“የዚህን ቅዱስ ሳምንት መነሻ በማድረግም፣ በጦርነቱ እየተሳተፉ ያሉ ሁሉም ወገኖች እና በዓለም ዙሪያ ላሉ የሰላም አምባሳደሮች የትንሳኤ ጥሪዬን እንድትቀላቀሉ እጠይቃለሁ” ሲሉም ተናግረዋል።
“የሰዎችን ህይወት እንታደግ፤ ደም መፋሰስ እና የሀገራት ውድመት ይቁም” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ጉቴሬስ ባቀረቡት ጥሪም የተኩስ አቁሙ በነገው እለት ማለትም በፀሎተ ሀሙስ እስከ እሁድ የትንሳዔ በዓል (የፋሲካ) እለት ድረስ እንዲዘልቅም ጠይቀዋል።
ዩክሬን ሩሲያ የጉቴሬዝን ጥሪ እንድትቀበል ወዲያውኑ የጠየቀች ሲሆን፤ በተመድ የሩሲያ መልእክተኛ በበኩላቸው የጉቴሬዝ ጥሪ “አጠራጣሪ” ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ሩሲያ በተለያ ጊዜያት የሰብአዊነት ኮሪደሮችን መፍጠሯን ያስታወቁት የሩሲያ መልእክተኛ፤ ዩክሬን እድሉን በአግባቡ ሳትጠቀም ቀርታለች ሲሉም አስታውቀዋል።
አብዛኛው ዩክሬናውያን የኦርቶዶክ እምነት ተከታዮች እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ።