ፖለቲካ
ቦርዱ አጠቃላይ የምርጫ ጊዜያዊ ውጤትን በተለያዩ ምክንያቶች ይፋ ማድረግ አለመቻሉን ገለጸ
አጠቃላይ የምርጫው ጊዜያዊ ውጤትን በ10 ቀናት ውስጥ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ተገልጾ ነበር
73 የሚሆኑ የምርጫ ክልሎች ጊዜያዊ ውጤቶች ዛሬ በቦርዱ ድረ ገጽ ላይ ይፋ ይደረጋል
አጠቃላይ የምርጫ ጊዜያዊ ውጤትን በተለያዩ ምክንያቶች ይፋ ማድረግ አለመቻሉን የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
ቦርዱ አጠቃላይ የምርጫ ጊዜያዊ ውጤት በ10 ቀናት ውስጥ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ከዚህ ቀደም መግለጹ ይታወቃል።
የቦርዱ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፤ አጠቃላይ የምርጫ ጊዜያዊ ውጤት ዛሬ ይፋ መደረግ እንደነበረበት በመግለጽ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ውጤቱን ይፋ ማድረግ እንዳልተቻለም አስታውቀዋል።
የመራጮች ድምጽ መደመር ሂደቶች አለመጠናቀቅ እና በትራንስፖርት ችግር ወደ ማዕከል ውጤት ተጠቃሎ አለመድረስ ለውጤቱ መዘግየት በምክንያትነት አንስተዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በውጤት ላይ የሚያነሱት አቤቱታዎች ጊዜያዊ ውጤቶች ይፋ እንዳላደርግ ምክንያት እንደሆነም ሰብሳቢዋ ገልጸዋል።
ዋና ሰብሳቢዋ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በዛሬው መግለጫው በኦሮሚያ እና በአማራ ክልል የተወሰኑ የምርጫ ክልሎች የተረጋገጡ የምርጫ ውጤቶችን ይፋ አድርገዋል።
በአጠቃላይ 73 የሚሆኑ የምርጫ ክልሎች ጊዜያዊ ውጤቶች በዛሬው እለት በቦርዱ ድረ ገጽ ላይ ይፋ እንደሚደረገም ገልጸዋል።