በነጌሌ ምርጫ ክልል የግል ተወዳዳሪው “በኔ ምክንያት ምርጫ አይስተጓጎል” በማለታቸው ሂደቱ እንዲቀጥል ተወሰነ
ቦርዱ የግል ተወዳዳሪ ቅሬታ ማቅረባቸውን ተከትሎ ምርጫው እንዳይካሄድ ተወስኖ ነበር
በነገሌ ምርጫ ክልል 139 ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን፤ ምርጫ የተካሄደው በ105 ጣቢያዎች ነው
በኦሮሚያ ክልል ነገሌ ምርጫ ክልል አንድ ዕጩ ፎቶግራፋቸው እና ስማቸው አለመካተቱን ለምርጫ ቦርድ በማመልከታቸው ታግዶ የነበረው ምርጫ እንዲያዝ ተወሰነ።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ፤ ቦርዱ የግል ተወዳዳሪው ያቀረቡትን ቅሬታ ተከትሎ እንዳይካሄድ ወስኖ እንደነበረ አስታውሰዋል።
ይሁን እንጅ ቦርዱ ምርጫው እንዳይካሄድ የጣለውን የክልከላ መልዕክት በተለያዩ ምክንያቶች በመዘግየታቸው ምርጫው በ105 የምርጫ ጣቢያዎች መካሄዱ አስታውቀዋል።
አሁን ግን የግል ተወዳዳሪው በእርሳቸው ምክንያት ምርጫው እንዲስተጓጎል እንደማይፈልጉ ማመልከታቸውን የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚዴቅሳ ገልጸዋል።
የግሉ ተወዳዳሪው ምርጫው “በኔ ምክንያት ምርጫ አይስተጓጎልም” በማለት ምርጫው እንዲቀጥል በጹሑፍ ማሳወቃቸው የተገለጸ ሲሆን ቦርዱ አነጋግሯቸዋል ተብሏል።
በዚህም መሰረት የግል ዕጩው በነጻ ፈቃዳቸው ውሳኔ በማሳለፋቸው በምርጫ ክልሉ፤ ምርጫ ባልተደረገባቸው ጣቢያዎች ምርጫው በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚካሄድ ሰብሳቢዋ ተናግረዋል፡፡
በነገሌ ምርጫ ክልል 139 ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን ምርጫ የተካሄደባቸው በ105 ጣቢያዎች ነው።
ምርጫ የተደረገባቸው የ105 ምርጫ ጣያዎች ውጤትም እንደሚያዝ ያስታወቁ ሲሆን፤ በቀሪ 34 የምርጫ ጣያዎች ደግሞ በጥቂት ቀናት ውስጥ የሚካሄድ ይሆናል።