በሱዳን ግጭት በሽህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውንና ከአራት ሚሊዮን በላይ ደግሞ መፈናቀላቸውን ተመድ አስታውቋል
በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በሱዳን ጦር ኃይሎች እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል በተባባሰው ግጭት ከባድ ውጊያ ቀጥሏል።
ጦሩ ማክሰኞ ምሽት በማህበራዊ የትስስር ገጹ ባወጣው መግለጫ፤ ከካርቱም በስተደቡብ በሚገኘው ወታደራዊ ካምፕ ላይ የፈጥኖ ደራሹ ተዋጊዎች በድጋሚ ጥቃት አድርሰዋል ብሏል።
ጦሩ ይህን ጥቃት በመመከት በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ማድረሱንም ተናግሯል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በበኩሉ የወታደራዊ ካንፑን አንዳንድ ክፍሎች መቆጣጠሩን እና ከፍተኛ መጠን ያላቸውን የጦር መሳሪያዎች መያዙን አስታውቋል።
የሳዑዲ አረቢያው አል አረቢያ ቴሌቪዥን እንደዘገበው ግን ወታደራዊ ካምፑ ከሦስት ቀናት ከባድ ውጊያ በኋላ በጦሩ ቁጥጥር ስር ነው።
በዋና ከተማይቱ ካርቱም እና አጎራባች በሆኑት ኦምዱርማን እና ባህሪ እንዲሁም ግጭት በተከሰተባቸው ምዕራባዊ ዳርፉር አንዳንድ አካባቢዎች በሁለቱ ኃይሎች መካከል የሚደረገው ውጊያ ተባብሷል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በግጭቱ በሽህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
ተመድ ባለፈው ሚያዝያ በተቀሰቀሰው ግጭት ከአራት ሚሊዮን በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውንም አስታውቋል።