ዶ/ር እሌኒ ገብረመድህን በተመድ የልማት ፕሮግራም ኃላፊነት ተሰጣቸው
ኢትዮጵያዊቷ ዶ/ር እሌኒ የድርጅቱ የአፍሪካ ዋና የፈጠራ ኦፊሰር በመሆን ነው የተመረጡት
ዶ/ር እሌኒ የኢትዮጵያ ምርት ገበያን ና ብሉ ሙን የተባሉ ተቋማትን መመስረታቸው ይታወቃል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ኢትዮጵያዊቷን እሌኒ ገብረመድህንን (ዶ/ር) የድርጅቱ የአፍሪካ ዋና የፈጠራ ኦፊሰር በመሆን መምረጡን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ በስራ ዕድል ፈጠራ የሚታወቁት እሌኒ ገብረመድህን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ምርት ገበያን እና ብሉ ሙን የተሚባሉ ተቋማትን መመስረታቸው የሚታወቅ ሲሆን በተመድ የልማት ፕሮግራም አዲሱን ሥራቸውን በኒውዮርክ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል።
- ኢትዮጵያ በየዕለቱ ከ1 ሺህ ቶን በላይ ቡና ወደ ውጭ አገራት እየላከች መሆኑ ተገለጸ
- ኢትዮጵያ፤ ፈረንሳይ እና ቻይና ላቋቋሙት የብድር ኮሚቴ አዲስ የእዳ ሽግሽግ ጥያቄን አቀረበች
የዲጂታል ስራን ማቀላጠፍ እና ወደፊት አፍሪካን የሚመሩ ወጣቶችን ማብቃት ከተመድ የልማት ፕሮግራም የሚጠበቁ ስራዎች መሆቸው የገለጸው ድርጅቱ አዲሷ የአፍሪካ ዋና የፈጠራ ኦፊሰርም እነዚህን ስራዎች ለማቀላጠፍ እና ለማቀጣጠል ትልቅ ሚና እንደሚኖረው ገልጿል።
የተመድ ረዳት ዋና ጸሐፊ እና የተመድ የልማት ፕሮግራም ረዳት አስተዳዳሪና የአፍሪካ ሪጅናል ዳይሬክተር አሁና ኢዚአኮንዋ ድርጅቱ ከእሌኒ ገብረመድህን (ዶ/ር) ሙያዊ ልምዶች ብዙ እንደሚጠቀምና እርሳቸውም በመሾማቸው ደስተኛ እንደሆኑ ገልጸዋል።
እሌኒ ገብረመድህን (ዶ/ር) ከስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የሶስተኛ ዲግሪ አግኝተዋል።
እሌኒ ገብረመድህን (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ምርት ገበያን በ2000 ዓ.ም እንዲመሰረት ያደረጉ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በቢሊየን ዶላር የሚቆጠሩ የግብርና ምርቶችን ለገበያ ያቀርባል።