አጠቃላይ የምግብ ዋጋ ግሽበት በተጠናቀቀው የነሐሴ ወር የ37 ነጥብ 6 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ ተገለጸ
ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሶች የዋጋ ግሽበት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር የ20 ነጥብ 8 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም ነው የተነገረው
የወሩ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር የ30 ነጥብ 4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም ተገልጿል
በተጠናቀቀው የነሐሴ ወር የነበረው አጠቃላይ የምግብ ዋጋ ግሽበት 37.6 በመቶ ሆኖ ተመዘገበ፡፡
የነሐሴ ወር 2013 ዓ/ም አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር በ30.4 ከመቶ ከፍ ብሎ እንደነበርም አል ዐይን አማርኛ ከማዕከላዊ ስታትስቲክስ ያገኘው መረጃ አመልክቷል፡፡
የዋጋ ግሽበት ሁኔታ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር በማነፃፀር የሚገኘው ውጤት ወቅታዊ የዋጋ ግሽበት ሁኔታን ይገልጻል፡፡
በዚህ መሰረት የምግብ ዋጋ ግሽበት የነሐሴ ወር 2013 ዓ.ም ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር 2012 ዓ.ም ጋር ሲነፃፀር በ37.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
በዳቦና እህሎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ በያዝነው ወር ተጠናክሮ የቀጠለም ሲሆን በተለይ የሩዝ፣ የእንጀራ፣ የዳቦ፣ የጤፍ፣ የስንዴ፣ የማሽላ፣ የበቆሎ፣ የገብስ፣ የስንዴ ዱቄት፣ የፓስታና ማካሮኒ ዋጋ በፍጥነት ጨምሯል፡፡
በተጨማሪም ሥጋ፣ የምግብ ዘይት፣ ወተት፤ አይብና ዕንቁላል፤ ቅቤ፣ ቅመማ ቅመም (ጨውና በርበሬ) እና ቡና የዋጋ ጭማሪ በዚህም ወር በመቀጠላቸው ለዋጋ ግሽበት ምጣኔ በፍጥነት መጨመር አስተዋጽኦ አድርገዋል።
ያለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወር ዋጋ ከአሁኑ ዓመት ተመሳሳይ ወር ጋር በንጽጽር ዝቅተኛ ስለነበር የዋጋ ግሽበቱ በያዝነው ወርም ከፍ ብሏል፡፡
በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት የነሐሴ ወር 2013 ዓ.ም ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር 2012 ዓ/ም ጋር ሲነፃፀርም የ20.8 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡
ከምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ በተለይም በአልኮልና ትምባሆ፣ ልብስና ጫማ፣ አነቃቂዎች (ጫት)፣ የቤት እንክብካቤና ኢነርጅ (ማገዶና ከሰል)፣ የቤት መስሪያ እቃዎች (የቤት ኪራይ፣ሲሚንቶ፣የቤት ኪዳን ቆርቆሮ)፣ የቤት ዕቃዎችና የቤት ማሰገጫዎች)፣ ህክምና እና ጌጣጌጥ (ወርቅ) ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ ነው፡፡