የሴቶች እና ህጻናት ሚኒስትሯ ፊልሰን አብዱላሂ የስራ መልቀቂያ አስገቡ
ለህሊናዬ በሚከብዱ ባሏቸው ግላዊ ምክንያቶች ምክንያት የመልቀቂያ ደብዳቤውን መጻፋቸውንም አስታውቀዋል
ሚኒስትሯ በሰው ሃይል እና በጀት እጦት እምብዛም ይሰራ ያልነበረውን መስሪያ ቤት የመምራቱን ሃላፊነት መረከቡ ለውድቀት እንደመመቻቸት ሆኖ ነው የተሰማኝ ብለዋል
የሴቶች፣ህጻናት እና ወጣቶች ሚኒስትሯ ፊልሰን አብዱላሂ የስራ መልቀቂያ አስገቡ።
በዕድሜ ትንሿ የካቢኔ አባል ዛሬ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መልቀቂያ ማስገባታቸውን በተለያዩ የማህበረሰብ ገጾቻቸው አስታውቀዋል።
ሚኒስትሯ በሰው ሃይል እና በጀት እጦት እምብዛም ይሰራ ያልነበረውን መስሪያ ቤት የመምራቱን ሃላፊነት መረከቡ ለውድቀት እንደመመቻቸት ሆኖ ነው የተሰማኝ ሲሉ በገለጹበትና ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጻፍኩ ባሉት ደብዳቤያቸው በችግሮች መካከልም ቢሆን የተቋሙን የ10 ዓመታት እቅድ ከማዘጋጀት ጀምሮ ባለፈው አንድ ዓመት ትልቅ ጥረትን ስናደርግ እንደነበር በኩራት ለመናገር እችላለሁ ብለዋል፡፡
በማንኛውም የስራ ጫና እና ውጥረት ውስጥ ሆነን መቼ እንስራ እና መቼ እንልቀቅ በሚል የሚያጋጥሙ ልዩነቶችን እንደሚቀበሉ ተስፋ አደርጋለሁ ሲሉም ነው ፊልሰን በደብዳቤያቸው ያሰፈሩት፡፡
ስነ ምግባሬን የተመለከተ ማንኛውም ሁኔታ ከእምነት እና እሴቶቼ የተቃረነ ነው ያሉም ሲሆን ይህን አሳልፎ መስጠት ለራሴ እና ለዜጎች ያለኝን እምነት መጣስ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ለህሊናዬ በሚከብዱ ባሏቸው ግላዊ ምክንያቶች ምክንያት የመልቀቂያ ደብዳቤውን መጻፋቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቋሙን እንዲመሩ ለሰጧቸው እድልም አመስግነዋል፡፡
ወ/ሮ ፊልሰን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አቅራቢነት መጋቢት 3/2012 ዓ.ም የሴቶች፣ህጻናት እና ወጣቶች ሚኒስትር ሆነው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሾማቸው የሚታወስ ነው፡፡