"77 ሳይደገም ፣ ህዝብ ሳይሰደድ መንግስት በአስቸኳይ ይድረስልን" በአንበጣ የተጎዱ አርሶአደር
ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶአደሮች የዕለት ምግብ ድጋፍ ማጓጓዝ እንደተጀመረ ተገልጿል
በምስራቅ አማራ በሠብል ከተሸፈነው 998 ሺ 517 ሄክታር መሬት 4.5 በመቶ ያህሉ በአንበጣ ተጎድቷል
"77 ሳይደገም ፣ ህዝብ ሳይሰደድ መንግስት በአስቸኳይ ይድረስልን" በአንበጣ የተጎዱ አርሶአደር
በምስራቅ አማራ የበረሃ አንበጣ መንጋ በሰሜን ወሎ ቆቦ ፣ ሃርቡ እና ወርቄ ፤ በደቡብ ወሎ ወረባቦ ፣ ተሁለደሬ እና አርጎባ ፤ በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን በባቲ ፣ በደዌ ሃረዋ በአርጡማ ፉርሲ እንዲሁም በሰሜን ሸዋ በቀወት እና ለአፋር ቅርበት ባላቸው አጎራባች አካባቢዎች ተከስቷል፡፡
የአንበጣ መንጋው የአርሶ አደሩን የሰብልና የቋሚ ተክል ዝሪቶች አውድሟል ፤ በርካቶችንም ላልተጠበቀ ችግርና ዱብዳ ዳርጓል። ለአብነትም በደቡብ ወሎ ብቻ በአጠቃላይ 54,997 የቤተሰብ አባላት ያሏቸው 9,759 አባወራና እማወራ አርሶአደሮች ሰብላቸው ተጎድቷል፡፡
ከ30 ለሚልቁ አመታት ከኖሩበት የኦሮሚያ ክልል ኢሉባቡር አካባቢ ተፈናቅለው ከ3 ዓመታት በፊት ወረባቦ ወረዳ 015 ተብሎ ወደሚጠራው ቀበሌ የመጡት አርሶአደር መሃሙድ ሃሺም ፣ የዘንድሮው ችግር ቀደም ሲል ከገጠሙን የተለየ ነው ይላሉ።
“ህጻን ሆነን በኃይለስላሴ ጊዜ የተመለከትነው ችግር ከዚህ ይቀል ይሆን?” ሲሉ ራሳቸውን ይጠይቃሉ።
በረመዳን የጾም ወቅት አርሰው የዘሩት ሰብል ወድሟል፡፡ የሰዉ ብቻ ሳይሆን የእንስሳቱም ምግብ መውደሙን አርሶአደር መሃሙድ ገልጸዋል፡፡
"የአካባቢው ህዝብ ተፈናቅዬ ስመጣ ያገራችን ልጅ እንኳን ሳትሞት በደህና መጣህ ብሎ የተቀበለኝ እህል ቢኖር ነው ፤ ዛሬማ እህል ከሌለ እኔን ባዳውን ይቅርና ልጆቹን ሁሉ የሚያስጥል ጊዜ መሆኑን በ77 አይተናል" ሲሉ ነው የ8 ቤተሰብ አስተዳዳሪው የ65 ዓመቱ አዛውንት የሚናገሩት።
"ሰው ልጁን እየተወ የተሰደደበት ጊዜ (77) ሳይደገም ፣ ለመፈናቀልና ለስደት ሳይዳረግ ፣ መንግስት በአስቸኳይ እንዲደርስላቸውና እንዲያቋቁማቸው" ጠይቀዋል፡፡ መጪውን የበልግ ወቅት የአካባቢያቸውን የውሃ ሃብት ተጠቅመው ማልማት እንዲችሉ ድጋፍ እንዲደረግላቸውም ነው የጠየቁት።
በተለይም ለመስኖ በሚል ተቆፍረው ነገር ግን ያለተግባር ታሽገው የተቀመጡ የውሃ ጉድጓዶች ቢከፈቱላቸው አልምተው ራሳቸውን ለመታደግ እንደሚችሉም ገልጸዋል።
አንበጣ የጤፍ ሰብላቸውን ያወደመባቸው አርሶአደር ሳሩን ለከብቶች እያጨዱ
ከፌዴራል እና ከአማራ ክልል የተውጣጡ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ጎብኝተዋል፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ ለተጎጂዎች አስቸኳይ የዕለት ምግብ ለማድረስ ማጓጓዝ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ ደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦና ሌሎችም አካባቢዎች ተቆፍረው ነገር ግን ተዘግተው የተቀመጡ የውሃ ጉድጓዶች ወደስራ እንደሚገቡም ነው የገለጹት፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ
የበረሃ አንበጣ መንጋው በምስራቅ አማራ 4 ዞኖች መከሰቱን ገልጸው በዞኖቹ ከሚገኙ 69 ወረዳዎች መካከል በ20 ወረዳዎች 151 ቀበሌዎች ውስጥ ተከስቶ ጉዳት ማድረሱን ተናግረዋል፡፡
እንደ ኃላፊው ገለጻ በክልሉ ምስራቃዊ ክፍል በሠብል ከተሸፈነው 998 ሺ 517 ሄክታር መሬት 4.5 በመቶ ያህሉ ነው ጉዳት የደረሰበት፡፡ አጠቃላይ የጉዳቱ መጠን ጥናት ያስፈልገዋል ተብሏል፡፡
በክልሉ በዘንድሮው የምርት ዘመን ከ127 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዷል ፤ ዝናቡም የተሻለ መሆኑ እቅዱን ለማሳካት እንደሚረዳ ነው የገለጹት፡፡
በአንበጣ የተጎዳውን ደግሞ በመስኖ ጭምር ለማካካስ ታቅዷል፡፡
አንበጣውን ለመከላከል በ3 አውሮፕላኖች ርጭት እየተደረገ የቆየ ሲሆን ፣ አንዷ ወረባቦ ላይ መከስከሷ ይታወሳል፡፡
አቶ ተስፋሁን እንዳሉት የሚመጡት አውሮፕላኖች የመከላከል አቅማችንን እንደሚያሳድጉ ቢጠበቅም ዋናው ግን የህዝቡ ስራ ነው፡፡
በምስራቅ አማራ መንጋውን በመከላከል ረገድ የህዝቡና የባለሙያ ድጋፍ ከፍተኛ ነው ያሉት የግብርና ሚኒስትር ዴዔታ አቶ ወንዳለ ሃብታሙ 4 ሺ 177 ባለሙያዎች እንደተሰማሩ ገልጸዋል፡፡
በ151 ቀበሌዎች 45 ሺ 350 ሄክታር መሬት በአውሮፕላን ኬሚካል ተረጭቷልም ነው ያሉት፡፡ ከአሁን ቀደም መንጋው በአፋር እያለ ከፍተኛ ርብርብ ባይደረገ ኖሮ ወደ ደጋማ አካካባቢዎች ይዛመትና የከፋ ጉዳት ያደርስ እንደነበርም ነው የጠቀሱት፡፡
የምግብ እጥረትን ለመሙላት የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ይደረጋል ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል የአውሮፕላን ርጭቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በጉብኝቱ የተገኙት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ የተመለከቱትን ለፌዴራሉ መንግስት እንደሚያሳውቁና አስፈላጊው ድጋፍ በአስቸኳይ እንደሚደረግ አብራርተዋል።
ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ከጉብኝት በኋላ ለጋዜጠኞች ገለጻ ሲሰጡ
የወሎ ዩኒቨርስቲ የአመራር አካላትም ለአርሶ አደሩ መኖ ሊያዘጋጅ የሚችልበትን ሙያዊ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።