የአንበጣ መንጋው በሰሜን ሸዋ ዞን ከሚገኙ 24 ወረዳዎች በ17ቱ ላይ መከሰቱ ተገልጿል
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የአንበጣ መንጋ ተከሰተ
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የአንበጣ መንጋ መከሰቱን የዞኑ አስተዳደር አስታወቀ፡፡ መንጋው በአንጾኪያ ገምዛ፣አንኮበር ፣ መንዝ ቀያ ፣ ግሼ ራቤል ፣ ቀወት ፣ በሸዋሮቢትና በሌሎች አካባቢዎች መታየቱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታውቋል፡፡
የመምሪያው ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት ኃይሌ እንደገለጹት እስካሁን በዞኑ ከሚገኙ 24 ወረዳዎች በ17ቱ ውስጥ ባሉ 125 ቀበሌዎች የአንበጣ መንጋው ተከስቷል፡፡ መንጋው በማሳ ሰብሎች እና እጽዋት ላይ በተለያዩ ቦታዎች ከ0 ነጥብ 8 እስከ 22 በመቶ ጉዳት ማድረሱን የገለጹት የመምሪያው ኃላፊ ፣ አሁን ላይ በሰው ኃይልና በኬሚካል መንጋውን ለማጥፋት እየተሰራ መሆኑን ለአል ዐይን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 2 ሺ ሊትር ኬሚካል ከነመርጫ መሳሪያው ከፌዴራል መንግስት ድጋፍ መገኘቱን ያነሱት ወ/ሮ መሰረት ሁኔታው በዚሁ ከቀጠለ ወደ ደቡብ ወሎ ዞንና ወደ ኦሮሚያ ክልል ሊዛመት እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ከዞኑ ነዋሪዎች ባገኘነው መረጃ መሰረት "አደገኛ" የተባለው ይህ የበረሃ አንበጣ መንጋ በአንፆኪያ ገምዛ ወረዳ ግሾጌ በተባለ ቀበሌ ብቻ 1,000 ሔክታር መሬት ወሯል፡፡ በመንጋው የተወረረውን የመሬት ስፋት በተመለከተ ጥያቁ ያነሳንላቸው ወ/ሮ መሰረት “አጠቃላይ በመንጋው የተወረረውን የቦታ ስፋት መጠን ጥናት አድርገን እንገልጻለን” ብለዋል።
በዞኑ እስካሁን መንጋው ያልተከሰተው በደብረ ብርሃን ፣ በባሶና፣ ሀገረ ማሪያም ፣ ሲያ ደብር ፣ ሞረትና ጅሩ ፣ ሚዳ ወረሞ እና እንሳሮ ወረዳ ናቸው ብለዋል፡፡
የአካባቢው አርሶአደሮች የአንበጣ መንጋውን በባህላዊ መንገድ ለማባረር ቢሞክሩም የሔደው እየተመለሰ እንዳስቸገራቸው ገልጸዋል፡፡ የአንበጣ መንጋውን ለማጥፋት በአፋርና በአማራ ክልል አዋሳኝ ቦታዎች ላይ የኬሚካ ርጭት እንደሚደረግም ተገልጿል፡፡
በሰኔ ወር 2011ዓ.ም በኢትዮጵያ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ የስርጭት አድማሱን አስፍቶ 175 የሚሆኑ ወረዳዎች ማዳረሱን የግብርና ሚኒስቴር ለአል ዐይን ገልጾ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የበረሃ አንበጣ መንጋ በብዛትና በፍጥነት እየተፈለፈለ ስለሆነ መንጋው እየጨመረ ሊሔድ እንደሚችልም ግብርና ሚኒስቴር ስጋቱን ገልጿል፡፡
ከኢትዮጵያ ባለፈ በአብዛኛው የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተከሰተው መንጋው ፣አስቸኳይ መፍትሔ ካላገኘ ፣ ወትሮውንም ለተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች እና ለምግብ ችግር ተጋላጭ የሆነውን ቀጣናውን ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ሊያጋልጥ እንደሚችል ተሰግቷል፡፡