ሰሜን ኮሪያ በዚህ ወቅት ለምን በደቡብ ጎረቤቷ ላይ ተኩስ ከፈተች?
ሰሜን ኮሪያ በዚህ ወቅት ለምን በደቡብ ጎረቤቷ ላይ ተኩስ ከፈተች?
ወትሮም ቢሆን ሰላም ያልነበረው ቀጣና ሊሻለው ነው ሲባል ሲብስበት፣ ተረጋጋ ሲባል የተኩስ ቦታ ሲሆን እየተስተዋለ ነው፡፡ ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ በኪም ጆንግ ኡንና ሙን ጃኢን መካከል በተደረገ የእጅ ሰላምታ ታሪክን ቀየሩት ሲባልም ነበር፡፡ ይሁንና አካባቢው ከዚህ ያለፈ ሰለማ እንደሚፈልግ ይገለጻል፡፡
ከሰሞኑ የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን የጤንነት ሁኔታ አሳሳቢ ሆኖ ቆይቷል፡፡ የአሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ባለስልጣነትም የኪምን ጤንነት በብርቱ ሲጠይቁ ቆይተዋል፡፡ አንዳንድ ሚዲያዎች ከሲኡል ባለሥልጣናት የኪምን ሞት የሚያረጋግጥ መረጃ አግኝተናል ሲሉ ዘግበው ነበር፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የልብ ቀዶ ህክምና አድርገው በህይውት አሉ ሲሉ ቆይተዋል፡፡
ይሁንና የሰሜን ኮሪያው ሰው ማዳበሪያ ፋብሪካ ለማስመረቅ በሚል ምክንያት በሃሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን መታየታቸው አስገራሚ ነበር፡፡ እርሳቸው በይፋ ከታዩ በኋላ ሃገራቸው ከደቡብ ኮሪያ በምትዋሰንበት ድንበር ላይ ወታደሮቻቸው ተኩስ ከፍተዋል፡፡
ከሰሜን ኮሪያ ለመጣው ተኩስ የሲኡል ሰዎች አጸፋ ሰጥተዋል፡፡ የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በሁለቱ ሃገራት ድንበር ከወታደር ነጻ በሆነው ቦታ ላይ ተኩስ መክፈቷን በመጀመሪያ ይፋ ያደረጉት የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት ናቸው፡፡
የደቡብ ኮሪያ ጦር አመራሮች የሰሜን ኮሪያ ወታደሮች በደቡብ ኮሪያዋ ቸወሮን በተሰኘች ከተማ ተኩስ ስለመከፈቱ አረጋግጠዋል፡፡ ይሁንና በተኩሱ ምንም ጉዳት አለመድረሱ ነው የተነገረው፡፡ የአጸፋ ተኩስና የማስጠንቀቂያ መልዕክትም ጭምር ለፒዮንግያግ ሰዎች ማስተላለፋቸውንም ደቡቦቹ የገለጹ ሲሆን የተኩሱ መነሻ ግን አልታወቀም ነው የተባለው፡፡ ይሁንና ከሰሜን ኮሪያ የተከፈተው ተኩስ ሆን ተብሎ እንደሆነ ነው የተገለጸው፡፡
ቢቢሲ ላይ የወጣው ዘገባ እንደሚያሳየው ሰሜን ኮሪያ ይህንን ተከስ የከፈተችው ሆን ብላ ሰሞነኛውን የኪምን መጥፋት ወሬ ለማስቀየር ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም ወታደራዊ ሃይሏ አሁንም ጠንካራ መሆኑን እንዲሁም በሰሜን ኮሪያ ኪም ህክምና ላይ ስለቆዩ የመዳከም ነገር ይታያል የሚል መንፈስ እንዳኖር ሊሆን እንደሚችልም ነው የተወራው፡፡
የሰሜን ኮሪያ ድርጊት በቀጣይ ድርድሮችም ጫና ለመፍጠርና አሁንም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆኖ ለመገኘት የተደረገ ሳይሆን እንደማይቀርም ነው የተገመተው፡፡ የጤንነት ሁኔታቸውን በተመለከተ ሞተዋል ወይስ በህይወት አሉ በሚል በሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ላይ አሉባልታዎች ሲወጡ የነበረ ቢሆንም እርሳቸው በቴሌቪዥን መስኮት ከታዩ በኋላ ግን በድንበሩ ተኩስ መሰማቱ ሰውዬውና የመሳሪያ ድምጽ አብሯቸው አለ አስብሏል፡፡ የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት በኪም የጤንነት ጉዳይ ሰሞኑን አስተያየት ሲሰጡ መቆየታቸውም ለተኩሱ መነሻ ሳይሆን አልቀረም የሚሉም አሉ፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ሰሜን ኮሪያ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ድረስ ማብራሪያ አልሰጠችም፡፡
የኪም ከሳምንታት በኋላ በአደባባይ መታየት ዓለምን ያነጋገረ ጉዳይ ሲሆን የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ኪም ጆንግ ኡን የልብ ቀዶ ህክምና ካደረጉ በኋላ ዳግም በአደደባባይ በበመታየታቸውና ከህክምና በመመለሳቸው ደስተኛ መሆናቸውን በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡