“አል-ሁስን” የተሰኘው ዲጂታል አፕሊኬሽን በስማርት ስልኮች እና መሰል ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች የሚሰራ ነው
“አል-ሁስን” የተሰኘው ዲጂታል አፕሊኬሽን በስማርት ስልኮች እና መሰል ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች የሚሰራ ነው
የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል የምታደርገውን ጥረት የሚደግፍ አዲስ መተግበሪያ (አፕሊኬሽን) ተግባር ላይ አውላለች፡፡
አል-ሁስን የተሰኘው ይህ መተግበሪያ በስማርት ስልኮች እና የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ላይ ተጭኖ የሚሰራ ነው፡፡ የሀገሪቱ የጤና እና ማህበረሰብ ጥበቃ ሚኒስቴር ከአቡ ዳቢ የጤና ባለስልጣን ጋር በመሆን ነው አፕሊኬሽኑን ወደ ስራ ያስገቡት፡፡
በታሪካዊው የአቡ ዳቢ ህንጻ ስም የተሰየመው አል-ሁስን መተግበሪያ በሀገሪቱ ቫይረሱን ለመከላከል በመንግስት የሚከናወኑ አዳዲስ ተግባራትን ለማግኘት ያስችላል፡፡ የኮሮና ቫይረስ ምርመራ የሚያደርጉ ግለሰቦችም ውጤታቸውን በዚሁ መተግበሪያ አማካኝነት ማግኘት ይችላሉ፡፡ እያንዳንዱ የመተግበሪያው ተጠቃሚ የየራሱ የፈጣን ምላሽ ኮድ ይኖረዋል፡፡ ይሄው መተግበሪያ የተጠቃሚዎቹን የጤና ሁኔታ በመከታተል መረጃ የሚሰጥ ሲሆን በዚህም በነጻነት ሰዎች ወደሚበዙባቸው ስፍራዎች ለመሄድ እና ከሰዋች ጋር ለመገናኘት እንዲችሉ ፈቃድ ይሰጣል ተብሏል፡፡
በኤሚሬቶች ኮቪድ-19ን ለመከላከል መንግስት የሚያደርገውን ጥረት የሚረዳውን አዲሱን መተግበሪያ ከ አይኦኤስ እና አንድሮይድ (IOS and Android) በነጻ በማውረድ (ዳውንሎድ በማድረግ) መጠቀም ይቻላል፡፡
የሀገሪቱ የጤና እና ማህበረሰብ ጥበቃ ሚኒስትር አብዱል ራህማን ቢን ሙሐመድ አል-ኦዌይስ እንዳሉት አል-ሁስን መተግበሪያ የሞባይል ስልክ የመጨረሻ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ኮቪድ-19ን ለመከላከል እገዛ ያደርጋል፡፡ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች መንግስት የሀገሪቱን ዜጎች እና ነዋሪዎች ደህንነት ለመጠበቅ የሚያስችሉትን ሁሉ ጥረቶች እንደሚያደርግም ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡