“የኢትዮጵያ መንግስት እና የህወሓት አመራር ለመደራደር የሚያስችል የሞራል እኩልነት የላቸውም”- ኃይለማሪያም ደሳለኝ
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የድርድር ጫና “ሁኔታውን በወጉ ካለመረዳት” የመጣ ነውም ብለዋል
ህወሓት በዓለም አቀፍ ጫና ለመደራደር የሚፈልገው አንድም ከተጠያቂነት ለማምለጥ ሁለትም ወደ ስልጣን ለመመለስ ነው
“የኢትዮጵያ መንግስት እና የህወሓት አመራር ለመደራደር የሚያስችል የሞራል እኩልነት የላቸውም”- ኃይለማሪያም ደሳለኝ
የኢትዮጵያ መንግስት እና የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) አመራር ለመደራደር የሚያስችል “የሞራል እኩልነት” እንደሌላቸው የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ አስታወቁ፡፡
አቶ ኃይለማርያም በፎሬይን ፖሊሲ መፅሔት ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የድርድር ጫና “ሁኔታውን በወጉ ካለመረዳት የመጣ ነው”ሲሉ ሞግተዋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያን ለመቅረብ እየሞከረ ያለው “በተሳሳተ የሞራል እኩልነት ግምት ነው”ም ነው አቶ ኃይለማሪያም በጽሁፋቸው ያሉት፡፡
ይህ ብዙዎቹን የውጭ ሃገራት መንግስታት ሁለቱን አካላት በተሳሳተ የሞራል ሚዛን እንዲመለከቱ እና እንዲወግኑ ማድረጉንም ደቡብ ሱዳንን በተምሳሌትነት አንስተው አብራርተዋል፡፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከነጻነት በኋላ የእርስ በእርስ ግጭት ውስጥ የገባችውን የደቡብ ሱዳንን ተፋላሚ ኃይሎች ለማደራደር እና አሁንም የኢትዮጵያን ጉዳይ ለመያዝ እያደረገ ያለው ጥረት “በተሳሳተ የሞራል እኩልነት ግምት የተቃኘ ነው”ም ብለዋል፡፡
የችግሮቹ መሰረታዊ መነሻዎች በእንዲህ ዓይነት መንገድ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚሳቱ ናቸው ያሉት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጥረቱ ገና ለፍሬ ሳይበቃ ተደርሰዋል የተባሉ ስምምነቶች በተፈረሙ ማግስት መጣሳቸውን በማሳያነት አስፍረዋል፡፡
በህወሓት የበላይነት የተገነባው ጥምረት (ኢህአዴግ) ሃገሪቱን በብልጣብልጥነት ላለፉት 27 ዓመታት ሲመራ ስለመቆየቱም በመመስከርም ነው ኑዛዜ አከል የምስክርነት ቃላቸውንም ያስቀመጡት፡፡
እንደ አቶ ኃይለማርያም ገለጻ ህወሓት በተከታታይ ህዝባዊ አመጾች ከስልጣን ከተወገደ በኋላ“ለእንዲህ ዓይነት ነገሮች ስስ ልብ እንዳለው”ለሚያውቀው ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ተደጋጋሚ ጥሪ የሚያቀርበው አንድም ከተጠያቂነት ለማምለጥ፣ ሁለትም በዓለም አቀፍ ጫና ወደ ስልጣን ለመመለስ ነው ፡፡
ፌዴራል መንግስቱ ላይ ጦር የመስበቁ ምክንያትም ይኸው ነው እንደ አቶ ኃይለማርያም ገለጻ፡፡
“የሞራልና የፖለቲካ እውነታዎች ተዘንግተው በዓለም አቀፍ ጫና ወደ ስልጣን ለመመለስ በማሰብ፤ የሃገሪቱ የመከላከያ ጦር ሊበግረው ምናልባትም ሊያሸንፈው የማይችል አቅም እንደገነቡ በማመን እና ጦሩ ተከፋፍሎ የፌዴራል መንግስቱን በቀላሉ እጅ ሊያደርጉ እንደሚችሉ በማሰብ”ጥቃቱን ፈጽመውታልም ብለዋል፡፡
ሆኖም ሁሉም ኢትዮጵያውያን ጦር የማይበግራቸው ናቸው፡፡
ይህ በመሆኑም ህወሓት በአሁን ወቅት ብሄራዊውን ጦር ለመመከት የሚችልበት አቅምም አጥቶ በሁሉም አቅጣጫ ተከቦ ይገኛል፡፡
ሰሜን እዝን በማጥቃትና ጦር መሳሪያዎቹን በመዝረፍ ትግራዋይ ባልሆኑ የጦሩ አባላት ላይ እጅግ አሰቃቂ ጥፋቶችን መፈጸሙ የቡድኑን ወንጀለኛ አባላት ለፍርድ ለማቅረብ ህዝብና መንግስት የጀመሩትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ይበልጥ እንደሚያበረታቸውም ነው አቶ ኃይለማርያም በጽሁፋቸው ያተቱት፡፡