በጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ጌጣጌጦቻቸውን ሽጠው የመሰረቱት “ባቡል ኸይር” ብዙዎችን ከርሃብ ታድጓል
በጎ ፈቃደኛ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ጌጣጌጦቻቸውን ሽጠው የመሰረቱት “ባቡል ኸይር” ብዙዎችን ከርሃብ ታድጓል፡፡
የ“እኛና እነርሱ” ድንበር የሌለው፣ በዘርና በጎሳ የማይገደብ ሰው በሰውነቱ ብቻ የሚለካበት ነው ሰብዓዊ የበጎ አድራጎት ስራ፡፡ የስያሜው መሰረትም ይሄው ነው-ሰብዓዊነት-ሰው ለሰው ሰው በመሆኑ ብቻ! በቃ ሌላ ምንም ምክኒያት አይሻም፡፡
የሰብዓዊ እርዳታ የተጀመረበትን መቼት ይህ ነው ብሎ መጥቀስ ባይቻልም፣ በተደራጀ መልኩ የተጀመረው ግን በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ በስዊዘርላንዳዊው ሄንሪ ዱናንት አማካኝነት እንደሆነ ይታመናል፡፡
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በብዛት፣ በመጠንና በአይነት እየጨመሩ መጥተው፣ አሁን ላይ በዓለማችን በርካታ ሰብዓዊ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ይገኛሉ፡፡
በኢትዮጵያም አሁን አሁን ሀገር በቀል ሰብዓዊ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ ከነዚህ አንዱ የሆነው “ባቡል ኸይር” የበጎ አድራጎት ድርጅት ከ500 በላይ ዜጎችን በየቀኑ ይመግባል፡፡
“ባቡል ኸይር” እንዴት ተመሰረተ?
የበጎ ስራ በር የሚል ትርጓሜ ያለው “ባቡል ኸይር” በ117 ኢትዮጵያውያን በጎ ፈቃደኛ ሴቶች ባለፈው መስከረም ወር መገባደጃ ላይ ነው የተመሰረተው፡፡ በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም አካባቢ በኪራይ ቤት ውስጥ ተመስርቶ እስከዛሬ አገልግሎቱንም እዚያው በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
ከአል-ዐይን አማርኛ ጋር ቆይታ ያደረገችው የ“ባቡል ኸይር” መስራችና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሀናን ማህሙድ፣ ጥቂት ጓደኞቿን በማስተባበር በሂደት የአባላትን ቁጥር አሳድገው ድርጅቱን መመስረታቸውን ገልጻለች፡፡
የድርጅቱ መነሻ የገንዘብ ምንጭ ደግሞ ከመስራች አባላት የተሰበሰቡ የተለያዩ ጌጣጌጦቻችው ተሽጠው የተገኘ ገንዘብ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ ብዙ ተፈናቃዮች መኖራቸው፣ የሰዉ የኢኮኖሚ ችግር፣ የዳቦ ጥያቄ መብዛት፣…ወዘተ ድርጅቱን ለመመስረት መነሻችን ነው ስትልም ሀናን ተናግራለች፡፡ አቅማችን በፈቀደው የተወሰኑትን እንኳን ብንታደግ ብለን ከጓደኞቼ ጋር ተመካክረን ነው የጀመርነው፤ ያለችው “ባቡል ኸይር”፣ አላማው አድርጎ የተነሳው 1,000 ሰዎችን ለመመገብ ነው፡፡
በተመሰረተ በ 5 ወሩ ከ500 በላይ ሰዎችን የሚመግበው ድርጅቱ በየጊዜው ከሚጠበቀው በላይ ድጋፍ ፈላጊዎች በሩን እያንኳኩ ይገኛሉ፡፡ ይሄም ወ/ሮ ሀናን እና ጓደኖቿ ብዙ እንዲያቅዱ፣ ብዙም እንዲያልሙ እያስገደዳቸው ነው፡፡
ከድርጅቱ የምግብ አገልግሎት ተጠቃሚዎች መካከል
በርካታ አቅመ ደካሞች ደጁን ወደሚጠኑበት ወደዚህ ቤት ድንገት እግር ጥሎት ያቀና ብዙ የችግር አይነቶችን ያስተውላል፡፡ ከ“ባቡል ኸይር” ተገልጋዮች መካከል ወ/ሮ ሰሚራ አገዲ ትገኛለች፡፡ ሰሚራ የልብ፣የኩላሊት እና የነርቭ፣ ታማሚ ነች፡፡ ልቧ በተገጠመለት ባትሪ ነው የሚሰራው፡፡ የቀራት አንድ ኩላሊት ደግሞ በዳያልሲስ፡፡
ለማውራት ትንፋሽ እያጠራት እንዳወጋችን አራት ራሳቸውን ያልቻሉ፣ ተማሪ ልጆች አሏት፡፡ በምትኖርበት አዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ አምስት፣ በብርታቷ ዘመን በየቤቱ እየዞረች በቀን ስራ በምታገኘው ውስን ገቢ ልጆቿን ታስተዳድር ነበር፡፡ አሁን ግን ይሄን ማድረግ ተስኗታል፡፡ ህክምናዋም ኑሮዋም በድጋፍ ነው ሚሸፈነው፡፡ ለ21 ዓመታት በትዳር አብሯት የቆየው ባለቤቷም ፈተናዋ ሲበዛ ጥሏት መሄዱን ትገልጻለች፡፡
በመሸ እድሜያቸው የኤችአይቪ ታማሚ መሆናቸውን ያረጋገጡት ወ/ሮ ረውዳ ሲራጅ ሌላዋ የድርጅቱ ተመጽዋች ናቸው፡፡ 2ወንድና 2 ሴት በድምሩ 4 ልጆች አሏቸው፡፡
ከነዚህም ሁለቱ ጥለዋቸው ሲሄዱ ቀሪዎቹ ከአንድ የልጅ ልጃቸው ጋር በጠባብ ቤታቸው አብረዋቸው ይኖራሉ፡፡ ወ/ሮ ረውዳ እዚህ የሚያገኙት ድጋፍ ቢያንስ ጉሮሮአቸው ጾሙን እንዳያድር ረድቷቸዋል፡፡
ወደ ድርጅቱ ቅጥር ግቢ እየተመላለሱ ከሚመገቡት ውጭ የአልጋ ቁራኛ ታማሚዎች እና የአእምሮ ውስንነት ያለባቸው ኦቲስቶችም ቤት ለቤት ድጋፍ ከሚደረግላቸው መካከል ናቸው፡፡
ድርጅቱ በማን ይታገዛል?
“ባቡል ኸይር” የበጎ አድራጎት ድርጅት በቀን ሁለት ጊዜ ከሚመግባቸው ዜጎች በተጨማሪ ወደ ድርጅቱ መምጣት የማይችሉ አቅመ ደካሞችን ወደ ቤታቸው በመሄድ ይጠይቃቸዋል፡፡
ድርጅቱን የሚያገለግሉት አብዛኛው ሰራተኞች (መስራቾቹን ጨምሮ) ያለምንም ክፍያ በገዛ ፈቃዳቸው የሚያገለግሉ ናቸው፡፡ የተወሰኑ በክፍያ የሚያገለግሉ ሰራተኞችም አሉ፡፡
የቤት ኪራይ ወጪን ጨምሮ ባጠቃላይ አሁን ያሉትን የድርጅቱን አገልግሎት ተጠቃሚዎች ለመመገብ በወር በትንሹ ግማሽ ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚጠይቅ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
ወደተለያዩ አቅም ያላቸው ግለሰቦች ዘንድ በመሄድ ባደረጉት ተማጽኖ አሁን ላይ ድርጅቱን እንደየአቅማቸው የሚደግፉ ባለሀብቶች ቢኖሩም ይህ ግን ካለው ፍላጎት አንጻር በቂ አለመሆኑን የምትገልጸው ወ/ሮ ሀናን፣ ሁሉም እንደየአቅሙ ምግብ ነክ እና ከምግብ ውጭ የሆኑ ሸቀጦችንና ቁሳቁሶችን በመለገስ እጁን እንዲዘረጋ ተማጽናለች፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በ“ባቡል ኸይር” የበጎ አድራጎት ድርጅት ስም በተከፈቱ የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች በንግድ ባንክ 1000318219595፣ እንዲሁም በአዋሽ ባንክ 01410267076800 አማካኝነት የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ ይቻላል፡፡
ስለድርጅቱ ተጨማሪ መረጃ እና አድራሻውን ማግኘት የሚፈልግ በስልክ ቁጥር +251923276176 በመደወል ማብራሪያ መጠየቅ ይችላል፡፡