“ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ ተቋቁሞ በአጭር ጊዜ ተአማኒና ፍትሐዊ የሆነ ምርጫ አካሂደናል”- ጠ/ሚ ዐቢይ
ኢትዮጵያውያን ይወከሉናል የሚሏቸውን በመምረጣቸው ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆናለች ብለዋል
ተፎካካሪ ፓርቲዎች ስሕተቶችን በማረምና በመታገሥ ከፍ ያለ ሚና እንደተጫወቱም ገልጸዋል
በቀጣይ ቀናት የድምፅ ቆጠራ ተካሂዶ ውጤት እስኪገለጽ ምንም ዓይነት ችግሮች እንዳይፈጠሩ፣ እስካሁን በተመጣበት ሰላማዊ ሂደት እንዲቀጥልም ለሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ 6ኛው ሃገራዊ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት በሰላም መጠናቀቁን አስመልክተው የእንኳን ደስ አላችሁ መልእክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመልእክታቸውም፤ “ከየትኛውም ወገን ያልሆነ ገለልተኛ የምርጫ ቦርድ ተቋቁሞ፣ በአጭር ጊዜ ተአማኒና ፍትሐዊ የሆነ ምርጫ አካሂደን በስኬት አጠናቀናል” ብለዋል።
“ከአንግዲህ የምርጫው አሸናፊ ማንም ይሁን ማን፣ በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ወጥተው ይወከሉናል የሚሏቸውን ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ በመምረጣቸው ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆናለች” ሲልም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፤ “በአንዲት ምሽት ዴሞከራሲ ሆኖ የሚያድር ሀገር እንደሌለ አውቀን ለዴሞከራሲ ግንባታ ወሳኝ የሆኑ ጡቦችን ችላ ሳንል አንዱን በሌላው ጡብ ላይ እየደረደርን መጓዝ መማር አለብን” ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
“ከዚህ አንጻር ሲታይ የዘንድሮው ምርጫ በብዙ መልኩ ለዴሞክራሲ ግንባታ ወሳኝ ከሆኑ እርምጃዎች እንደ አንዱ ስለሆነ ልምዶቻችን ወደፊት ለምናደርጋቸው እልፍ ምርጫዎች ጥሩ መነሻ ተደርገው መወሰድ አለባቸው” ብለዋል።
“ለዚህ ምርጫ መሳካትና ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቅ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጫናዎችን ሁሉ ተቋቋማችኋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ ስሕተቶችን በማረምና በመታገሥ ከፍ ያለ ሚና እንደተጫወቱም ገልጸዋል።
“ለዴሞከራሲያዊ ልምምዳችን የመጀመሪያውን ጡብ በጋራ ስላስቀመጣትሁ ይህንን ተግባራችሁን ታሪክ ሲዘከረው ይኖራል” ብለዋል።
በምርጫው የትኛውም ፓርቲ ቢያሸንፍ፣ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ ሆኖ መጠናቀቁ በራሱ ከአንድ የምርጫ ዙር አሸናፊነት በላይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተር ዐቢይ፤ ይህም የዴሞከራሲ ልምምዳችንን አንድ ርምጃ ወደ ፊት የሚያስኬድ ስለሆነ ለሀገሪቱ ትልቅ ትርጉም ያለው ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል
ለምርጫ ቦርድ አመራሮችና ሠራተኞች እንዲሁም ለሚዲያዎች፣ ታዛቢዎች፣ የሲቪክ ማኅበራትና አጋር አካላት በሙሉ በኢትዮጵያ የዴሞከራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ታሪከ ሠርታችኋል፤ ያሉ ሲሆን ምስጋናም አቅርበዋል።
የጸጥታና ደኅንነት አካላት በሙሉ የምርጫው ሂደት ከተጀመረበት ዕለት አንሥቶ በያቅጣጫው የተከፈተውን ፈተና በማርገብ፣ ጸጥታ በማስከበር፤ ሕዝቡ ሰላምና ደኅንነት ተሰምቶት እንዲመርጥ ሌትና ቀን በሙሉም ምስጋና አቅርበዋል።
በመጨረሻም፣ በቀጣይ ቀናት የድምፅ ቆጠራ ተካሂዶ ውጤት እስኪገለጽ ምንም ዓይነት ችግሮች እንዳይፈጠሩ፣ እስካሁን በተመጣበት ሰላማዊ ሂደት እንዲቀጥልም ለሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ አቅርበዋል።
በልዩ ልዩ ምከንያቶች ምርጫ ያልተደረገባቸውን አካባቢዎች ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት፣ ዛሬ በተጀመረው መልኩ ምርጫ እንዲደረግባቸው የሁሉንም አካላት የላቀ ርብርብ ይፈልጋልም ብለዋል።