ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በሚወዳደሩበት ስፍራ ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን አቅርበዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ጎማ ወረዳ በሻሻ ተገኝተው እየተካሄደ ባለው አገራዊ ምርጫ ላይ ድምጻቸውን ሰጥተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በበሻሻ ከተማ በሚገኘው ጎማ ሁለት የምርጫ ክልል በበሻሻ ሶኬ ምርጫ ጣቢያ ተገኝተው ነው ድምጽ የሰጡት።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በወቅቱ በሰጡት መግለጫም፤ “ምርጫው በብዙ መለኩ ልዩ ነው፤ በዚህ ምርጫ መንግስት እና ህዝብን አምነው የተወዳደሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ክብር ይገባቸዋል” ብለዋል።
“ቢያሸንፉም ባያሸንፉም በዚህ ምርጫ ከውጭ ያለውን ጫና አንሰማም በማለት በምርጫው የተሳተፈ ሀይል ሁሉ ከብር እና ምስጋና ይገባቸዋል” ሲሉም ተናግረዋል።
“ምርጫ ቦርድ እንደ አዲስ የተቋቋመ እንደመሆኑ በየቦታው የሚያጋጥሙ የሎጅስቲክስ ጉዳዮች በቀር ከሞላ ጎደል በጣም ጠቃሚ ምርጫ እተካሄደ ነው፤ ቀጣይ ውጤቱን በጋራ የምናየው ይሆናል” ብለዋል።
ምርጫ ቦርድ የሚያጋጥሙ የሎጅስቲክ ችግሮችን ተቋቁሞ ምርጫውን ስኬታማ ለማድረግ የሄደበት ርቀት የሚያስመሰግነው እንደሆነም ገልፀዋል፡፡
በጎማ ሁለት የምርጫ ክልል ሁለት የፖለቲካ ፓርቲዎች እጩዎቻቸውን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ጋር እንዲፎካከሩ ማቅረባቸውም ይታወቃል።
በምርጫ ክልሉ ላይ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና እናት ፓርቲ ናቸው እጩዎቻቸውን ያቀረቡት።
በዚህም መሰረት አቶ ካሊድ ጀማል ሀይደር የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ)ን ወክለው በእጩነት የቀረቡ ሲሆን፤ አቶ ዳግም ዋሪሶ ካዎ ደግሞ እናት ፓርቲን ወክለው በእጩነት ቀርበዋል።