ኢትዮ-ቴሌኮም ተግባራዊ አደርገዋለሁ ያለው 5G ኔትዎርክ ምን የተለየ ያደርገዋል?
5G ከ4G ኔትዎርክ በእጅጉ ፈጣን ነው የተባለ ሲሆን፤ በሰከንድ ከ10 ጊጋ ባይት በላይ ፋይሎችን ለማውረድ ያስችላል
የ5G ኔትዎርክ እና በስራ ላይ ያለው 4G ኔትዎርክ ልዩነት ምንድን ነው?
ኢትዮ ቴሌኮም በአሁኑ ወቅት አለም የደረሰበትን አምስተኛ ትውልድ የሞባይል ኔትዎርክ (5G) አገልግሎት በዛሬው እለት ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቋል።
አምስተኛ ትውልድ የሞባይል ኔትዎርክ በዓለም ዙሪያ ወደ ስራ የገባው በፈረንጆቹ 2019 ላይ መሆኑ የሚነገር ሲሆን፤ በተለይም ባለው እጅግ የፈጠን የመጫን እና የማውረድ (ዳወንሎድ እና አፕሎድ) ፍጥነት በቴሌኮም ዘርፍ አዲስ አብዮትን ይዞ የመጣ ነው።
አምስተኛው ትውልድ የሚባለው 5G ኔትዎርክ ምንድነው?
አምስተኛው ትውልድ የሚባለው 5G ኔትዎርክ አሁን እደሉት 2G፣ 3G እና 4G ሁሉ የኔትዎር ዓይነት ሲሆን፤ አሁን የምንጠቀምበት ፈጣን የተባለውን አራተኛው ትውልድ የሚባለውን 4G በፍጥነቱ መቶ ጊዜ እጥፍ ይበልጠዋል።
5G ኔትዎርክ ከፍተኛ የኔትዎርክ ማሻሻያ እና መሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀሙ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ይህም የኔትዎርኩን ፍጥነት ከዓይን ጥቅሻ የፈጠነ ያደረገው መሆኑ ተነግሯል።
የ5G ኔትዎርክ ፍጥነት ጥቅሞች ውስጥም ምርታማነትን በማሻሻል የንግድ ሥራዎችን የበለጠ ውጤታማ እንደሚያደርግም ይጠበቃል።
የ5G እና 4G ኔትዎርክ ልዩነት ምንድን ነው?
በሁለቱ የኔትዎርክ አይነቶች መካከል ያለው ልዩነት ውስጥ “ፍጥነት” ዋነኛው ሲሆን፤ ቀላል እና ኃይል ቆጣቢ መሆኑም ከልዩነቶቹ ተጠቃሽ ነው።
የ5G ኔትዎርክ ፍጥነት በሰከንድ 10 ጊጋ ባይት (ጂ.ቢ) ሲሆን፤ ይህም አሁን በስራ ላይ ካለው 4G ኔትዎርክ በፍጥነቱ 100 ጊዜ እጥፍ እንዲበልጠው አድርጎታል።
ይህ ማለትም በ5G ኔትዎርክ ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያላቸውን ፊልሞች በሰከንዶች ውስጥ ለማውረድ የሚያስችለን ሲሆን፤ እንዲህ አይነት ጥራት ያላቸውን ፊልሞች ለማውረድ በ4G ኔትዎርክ እስከ አንድ ሰዓት ይወስዳል።
በተጨማሪም 4G ኔትዎርክ አንድ ትዕዛዝ ተቀብሎ ለማስተናገድ 0.045 ሚሊ ሰከንድ የሚፈጅበት ሲሆን፤ 5G ኔትዎርክ በተቃራኒው 0.01 ሚሊ ሰከንድ ይፈጅበታል።
አምስተኛው ትውልድ የሚባለው 5G ኔትዎርክ በፈረንጆቹ 2025 ላይም የዚህ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ቁጥር 1 ነጥብ 7 ቢሊየን እንደሚደርስ ይገመታል።