መንግስት የሰሜን ኢትዮጰያ ግጭት በሰላም እንዲፈታ ቁርጠኛ መሆኑን ለአሜሪካ አሳወቀ
አቶ ደመቀ መኮንን ከአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመር ጋር ተወያዩ
አሜሪካ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ለሚካሄደው የሰላም ድርድር ድጋፏን እንደምትቀጥል አስታውቃለች
የኢትዮጵያ መንግስት የሰሜን ኢትዮጰያ ግጭት በሰላም እንዲፈታ ቁርጠኛ መሆኑን ለአሜሪካ አሳወቀ።
አሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሀመር በአንድ ወር ልዩነት ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ መጥተዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን አዲስ አበባ ከመጡት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጋር መያየታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አቶ ደመቀ መኮን ከልዩ መልዕክተኛው ማይክ ሀመር ጋር ባደረጉት ውይይት የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜን የኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት በሰላም እንዲፈታ ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል።
ልዩ መልዕክተኛው አምባሳደር ማይክ ሀመር "አሜሪካ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ለሚካሄደው የሰላም ድርድር ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት በድርድር እንዲፈታ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙት የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሀመር በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት።
ልዩ መልእክተኛው ማይክ ሐመር በአሁኑ ጉዞዋቸው ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ወደ ናይሮቢ እና በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ በማቅናት በኢትዮጵያና እና በምስራቅ አፍሪካ ጉዳይ ከሀገራቱ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል።
ልዩ መልእክተኛው ማይክ ሐመር ባለፈው ነሃሴ ድጋሚ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ለማስቆም እና ድርድር እንዲጀመር ለማበረታታት አዲስ አበባ ሰንብተው ወደ ዋሽንግተን መመለሳቸው የሚታወስ ነው።
ማይክ ሐመርወደ አሜሪካ ከተመለሱ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ፤ ህወሓት እና በፌደራል መንግስት መካከል ያለውን ግጭት ለማስቆም ዋነኛ እንቅፋት የሆነው “በሁለቱም ወገኖች በኩል ያለው አለመተማመን ነው” ማለታቸው አይዘነጋም።
ጉዳዩ አሳሳቢ ቢሆንም ግን “የድርድር ተስፋ አለ”ም ነበር ያሉት ማይክ ሐመር።