ህወሓት ስለ ትግራይ ሕዝብ ሲል ለድርድር እንዲቀመጥ የቀረበውን ጥሪ ማክበር ይገባዋል- ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ
በ2015 የበጀት ዓመት ግጭቶችን በውይይትና በድርድር መፍታት የመንግስት ትኩረት መሆኑን ገልፀዋል
የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤትና የፌዴሬሽን ም/ቤት የጋራ የመክፈቻ ስነ ስርዓት ተካሂዷል
ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ "ህወሓት ስለ ትግራይ ሕዝብ ሲል የሠላም ጥሪውን በመቀበል ለድርድር እንዲቀመጥ የቀረበውን ጥሪ ማክበር ይገባዋል" ሲሉ አሳሰቡ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ተካሂዷል።
በመክፈቻው ላይም ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ የሀገሪቱን የ2015 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫ ዕቅድ ለምክር ቤቱ አባላት አቅርበዋል።
በንግግራቸውም በ2014 በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት እንዲሁም በአንዳንድ ቦታዎች በንፁሐን ዜጐች ላይ የደረሰው የጅምላ ጭፍጨፋ በአሉታዊ ጎናቸው የሚታወሱ ብቻ ሣይሆኑ የበርካቶችን ልብ የሰበረ መሆኑንም ገልፀዋል።
መንግስት ግጭት ጨርሶ እንዲያበቃ ከማንኛውም ወገን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለመደራደርና ልዩነቶችን በሠላምና በውይይት ለመፍታት ሀሳብ ማቅረቡን ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ አስታውሰዋል።
ይህንን ዕድል ስለ ትግራይ ሕዝብ ሲል ህወሓትም የሠላም ጥሪውን በመቀበል ለድርድር እንዲቀመጥ የቀረበውን ጥሪ ማክበር እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
በ2015 የበጀት ዓመት ግጭቶችን በውይይትና በድርድር በመፍታት፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሥራን ወደ ፊት በማራመድ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን በላቀ ደረጃ ማስቀጠል የመንግስት ትኩረት መሆኑንም ገልፀዋል።
በ2014 በጀት ዓመት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በዲኘሎማሲያዊ ዘርፎች ከዕቅዱ አኳያ ተስፋ ሰጪ ውጤት የተገኘበት መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።
በ2015 የኑሮ ውድነት ጫናዎችን ለማቅለል የተለያዩ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ያስታወቁ ሲሆን፣ መንግስት በተለይም ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ ጫናዎችን ለማቅለል እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።
ህዳሴ ግድብን በተመለከተም ግድቡ የመልማት ፍላጎታችንን እና ሌሎች ሀገራትን የመጉዳት ዓላማ እንደሌለን ያሳያንበት ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ፣ በ2015 የግድቡ ግንባታ በተያዘለት
እቅድ እንደሚከናወን እና ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር ድርድሮች እና ውይይቶችም ቀጥለው እንደሚካሄዱ አስታውቀዋል።
በተጨማሪም የሕዝቡን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ለመቅረፍ መንግስት በከፍተኛ ደረጃ የሚረባረብበት ዓመት እንደሚሆንፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በሀገሪቱ የ2015 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫ ዕቅድ አመላክተዋል፡፡