የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በኤሌክትሮኒክስ መስጠት እስከሚጀመር በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ይሰጣል ተባለ
ላለፉት ዓመታት የፈተና ስርቆት ትልቁ የትምህርት አጀንዳ ነበር
የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በቀጣይ በኤሌክትሮኒክስ እንደሚሰጥ መገለጹ ይታወሳል
የ 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንደሚሰጥ የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በሆሳዕና ፣ በወራቤና በወልቂጤ ከተሞች የሚገኙ ሁለተኛ ደረጃና ሞዴል ትምህርት ቤቶችን ሲጎበኙ ነው ይህንን ያሉት።
ሚኒስትሩ ከተማሪዎችና ከትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ጋር ባደረጉት ቆይታ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በትምህርት ቤቶች ሳይሆን በዩኒቨርስቲ ውስጥ ይሰጣል ብለዋል።
ፕ/ር ብርሃኑ፤ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በኤሌክትሮኒክስ መስጠት እስከሚጀመር ድረስ ፈተናው በዩኒቨርስቲዎች መሰጠቱ ይቀጥላል ብለዋል።
የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና በዩኒቨርስቲ እንዲሰጥ የተወሰነው የፈተና ሰርቆትና ማጭበርበርን ለማስቀረት ታስቦ በመሆኑ ተማሪዎች ትምህርት በስራና በታታሪነት የሚገኝ መሆኑን አውቀው በርትተው መማርና ማጥናት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትን ጥራትን ለማሻሻል በአጠቃላይና ከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፎች ሌሎችንም የተለያዩ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ መሆኑንም ፕ/ር ብርሀኑ ጠቁመዋል።
የ 12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በቀጣይ በኤሌክትሮኒክስ እንደሚሰጥ ቀደም ብሎ መገለጹ ይታወሳል።