ልዩልዩ
አብዛኞቹ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ከ350 በላይ ውጤት አምጥተዋል ተባለ
የዓመቱ ከፍተኛ ውጤት 669 ሆኖ መመዝገቡንም ነው ትምህርት ሚኒስቴር ያስታወቀው
702 ተማሪዎች ከ600 በላይ አምጥተዋልም ተብሏል
የ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናን ከግማሽ በላይ ተማሪዎች ከ350 በላይ ማምጣታቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ውጤትን በተመለከተ የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ መግለጫ ሰጥቷል።
የሀገር አቀፍ ትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) የ2012 ዓ.ም የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና በተመዝጋቢ፣ በተፈታኝም እንዲሁም በውጤትም ደረጃ ከፍተኛ መሆኑ ገልፀዋል።
ፈተናውን ከወሰዱ አጠቃላይ ተፈታኞች ውስጥ 55 ነጥብ 7 በመቶዎቹ ከ350 በላይ አምጥተዋል።
በመግለጫው የፈተና ውጤት ከባለፈው አመት ጋር ሲነፃፀር የተሻለ መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በዚህም ከ600 በላይ ያመጡ ተማሪዎች 702 መሆናቸው ተገልጿል።
የዓመቱ ከፍተኛ ውጤት 669 ሆኖ መመዝገቡንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል ።
ተማሪዎችም በፈተናዎች ኤጀንሲ ድረገፅ እንዲሁም በአጭር የፁሁፍ መልዕክት 8181 የፈተና መለያ ቁጥራቸውን በማስገባት ከነገ የካቲት 21 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ውጤታቸውን መመልከት እንደሚችሉ ተገልጿል።