ልዩልዩ
በትግራይ ክልል የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ፈተናውን በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ ይወስዳሉ ተባለ
ተፈታኞች በአካባቢያቸው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና ትምህርት ቢሮዎች ሪፖርት እንዲያደርጉ ተጠይቋል
የትምህርት መሰረተ ልማቶች ሙሉ ለሙሉ በመውደማቸው ነው ፈተናው በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚሰጠው
የትምህርት ሚኒስትሩ ጌታሁን መኩሪያ (ፒ ኤች ዲ) በትግራይ ክልል የሚገኙ ከ12ሺህ በላይ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞች በአካባቢው የትምህርት መሰረተ ልማቶች ሙሉ ለሙሉ በመውደማቸው ፈተናቸውን በአካባቢያቸው በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ እንደሚወስዱ ገልፀዋል፡፡
በዚህም መሰረት ከፊታችን ሰኞ ጀምሮ ተፈታኞች በአካባቢያቸው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች እና ትምህርት ቢሮዎች ሪፖርት እንዲያደርጉ ተጠይቋል፡፡
በሚቀጥሉት ሳምንታትም ተፈታኞችን በክልሉ ወደሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የማጓጓዝ ስራዎች እንደሚሰሩ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚያሳየው ተፈታኞቹ ፈተናቸውን የሚወስዱባቸው ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትም መቀሌ ፣ አክሱም ፣ አዲግራት እና ራያ የኒቨርስቲዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
የትምህርት ሚኒስትሩ የ 2012ዓ.ም ሀገር አቀፍ ፈተናን በተመለከተ በዛሬው እለት በሰጠው መግለጫ ፣ በኦንላይን ሊሰጥ የነበረው የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና መፈተኛ ታብሌቶች በግዜ ወደ ሀገር ውስጥ መግባት ባለመቻላቸው ፈተናውን በወረቀት ለመስጠት መወሰኑን ገልፀዋል፡፡