ኢሰመኮ ”ነጻ ሆኖ የመታየት መብትን” የሚጋፋ ተግባር መፈጸሙን የገለጹ የትግራይ ታሳሪዎች መኖራቸውን ገለጸ
ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤልና ባለሙያዎቹ እነ ስብሃት ነጋን ጨምሮ 21 ታሳሪዎችን ጎብኝተዋል
ኢሰመኮ ታሳሪዎቹ ወደ ፌደራል እስርቤት ከመጡ በኋላ ”ተገቢ ያልሆነ የእስር አያያዝ አለመኖሩን” ተናግረዋል ብሏል
ኢሰመኮ ባወጣው መግለጫ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ዳንኤልና ሌሎች ባለሙያዎቹ የካቲት 27 ቀን 2013 ዓ.ም. በእስር ቤት በመገኘት ከትግራይ ክልል ተጠርጥረው የተያዙትን ታሳሪዎችን ቅሬታ ሰምተዋል፡፡
መግለጫው ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤልና ባለሙያዎቹ እነ ስብሃት ነጋን ጨምሮ 21 ታሳሪዎችን መጎብኘታቸውንና አነጋግረዋል ብሏል፡፡
ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤልና ባለሙያዎቹ በጉብኝታቸው ወቅት ”በትግራይ ክልል ተጠርጥረው የተያዙትን እነ ዶ/ር አብረሀም ተከስተ፣ አምባሳደር አባይ ወልዱ፣ አቶ ስብሀት ነጋ፣ አምባሳደር አባዲ ዘሙ፣አቶ ቴዎድሮስ ሀጎስ፣ ዶ/ር ሰለሞን ኪዳኔ፣ ዶ/ር አዲስ አለም ባሌማ፣ ሜ/ጀነራል ይርዳው ገብረ መድኅን፣ ሜ/ጀነራል ገብረ መድኅን ፍቃዱ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም፣ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋን ጨምሮ በአጠቃላይ 21 ታሳሪዎች የሚገኙበትን የእስር ሁኔታ ጎብኝተው ታሳሪዎችን” ማነጋገራቸውን መግለጫው ጠቅሷል፡፡
መግለጫው ታሳሪዎቹ ከትግረይ ክልል ተይዘው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ “ነፃ ሆኖ የመገመት መብታቸውን በሚጋፋ መልኩ በሚዲያ አሰልፎ የማቅረብ እና የማንኳሰስ ሁኔታ እንደነበረ” ማንሳታቸውን ጠቅሷል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም “… ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለረጅም ጊዜ መቆየታቸውን፣ በትግራይ ክልል ከመቀሌ ከተማ ሸሽተው ሲሄዱ በተያዙበት ጊዜ ስድብ፣ ድብደባ፣ ማስፈራራት እና ተኩስ እንደነበረና የአካል መቁሰል እንደደረሰባቸው…”ተጠርጣሪዎቹ መናራቸውን መግለጫው ገልጿል፡፡
“በጉብኝቱም ታሳሪዎቹ በጥሩ አካላዊ ደኅንነት ላይ እንደሚገኙ፣ የሚገኙበት አካባቢና ክፍሎች ንፁህ እና ብዙም ያልተጨናነቁ፣ የተፈጥሮና የኤሌክትሪክ ብርሃን ያላቸው መሆኑንና አጠቃላይ ሁኔታው ተቀባይነት ያለው መሆኑን” ኢሰመኮ ገልጿል፡፡
ኢሰመኮ በመግለጫው ሁሉም ታሳሪዎች ወደ ፌደራል እስርቤት ከመጡ በኋላ ”ተገቢ ያልሆነ የእስር አያያዝ አለመኖሩንና ፖሊሶች በተገቢው የሙያ ሥነ ምግባር” እንሚሰሩ ታሳሪዎች ገልጸዋል ብሏል፡፡
“ታሳሪዎቹ የህክምና አገልግሎት ባለው አቅም እያገኙ እንደሆነ፣ ከቤተሰባቸው ተገናኝተው አቅርቦት እንደሚቀበሉ እና ከጠበቆቻቸው ጋር መገናኘት መቻላቸውን አስረድተዋል ያለው መግለጫው፤ የተወሰኑ ታሳሪዎች በመከላከያ ሠራዊት አባላት በትግራይ ክልል በበረሀ ውስጥ ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ በሰብአዊ እንክብካቤ መያዛቸውን እና የመከላከያ ሠራዊቱ አመራሮች ከድንገተኛ አደጋና ጥቃት እንደጠበቋቸው ገልጸዋል፡፡”
መግለጫው “አብዛኞቹ ታሳሪዎች የቀረበባቸው ክስ ፖለቲካዊ ነው ብለው እንደሚያምኑ፣ የተጠረጠሩበት ጉዳይ በተናጠል አለመቅረቡን እና የምርመራ ሂደቱ በአፋጣኝ አለመታየቱን ገልጸው አቤቱታ”ማቅረባቸውን ፈልጿል፡፡
ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ የወንጅል ምርምራው በፍጥነት እንዲጠናቀቅና በህጉ አግባብ በዋስትና ሊለቀቁ የሚገባቸውን እስረኞች መለየት እንደሚገባ ማሳሰባቸውን መግለጫው አንስቷል፡፡