በኦሮሚያ ክልል የፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ አለመከበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ እንዳሳሰበው ኢሰመኮ አስታወቀ
በዩኒቨርስቲው ፖሊሶች ተፈጽሞብኛል ያለው ድብደባ እንዲጣራም ኮሚሽኑ ጠይቋል
ኮሚሽኑ በጅማ ዩኒቨርስቲ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ የታሰሩ አመራሮች እንዲፈቱ በመጠየቁ የታሰረው ሙሃመድ ዴክሲሶ በአፋጣኝ እንዲፈታ ሲልም አሳስቧል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በጅማ ዩኒቨርስቲ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ የታሰሩ አመራሮች እንዲፈቱ በመጠየቁ የታሰረው ተመራቂ ተማሪ ሙሃመድ ዴክሲሶ በአፋጣኝ ከእስር ሊለቀቅ ይገባል ሲል አሳሰበ፡፡
የካቲት 6 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው ስነ ስርዓት ከተመረቁ የዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎች መካከል አንዱ የሆነው መሃመድ ከዘፋኙ የድምጽ ማጉያ ተቀብሎ ‘ጀዋር መሐመድ ይፈታ’፣ ‘ፍትሕ ለሀጫሉ ሁንዴሳ’ በማለቱ ነበር ከስነ ስርዓቱ በኋላ በዩኒቨርስቲው ፖሊሶች ተይዞ በከተማው ፖሊስ ጣቢያ ለመታሰር የበቃው፡፡
በተያዘ ጊዜ በዩኒቨርስቲው ፖሊሶች ድብደባ እንደተፈጸመበትም ለኮሚሽኑ አስረድቷል፡፡
ሙሃመድ የፈጸመው ተግባር ሊያስነቅፍ ወይም ሊያስወቅስ ቢችልም ለወንጀል ክስና ለእስር የሚያበቃ አልነበረም ያለው ኮሚሽኑ በዋስ እንዲለቀቅ በወረዳው ፍርድ ቤት ከተወሰነ በኋላ ወዲያወኑ አለመለቀቁ አሳስቦኛ ብሏል፡፡
ድርጊቱ የተደራረበ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በመሆኑ ሙሃመድን ጨምሮ በፍርድ ቤት የዋስትና መብት ተከብሮላቸው በእስር ላይ የሚገኙ ሌሎች እስረኞችም ጭምር በአፋጣኝ እንዲለቀቁም ነው ያሳሰበው።
እስረኛው ወደ ጅማ ፖሊስ መምሪያ ከመወሰዱ አስቀድሞ በፖሊሶች ተፈጽሞብኛል ያለውን ድብደባ በተመለከተ ተገቢው ማጣራት ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥም ኢሰመኮ ጠይቋል።
“በኦሮሚያ ክልል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የፍርድ ቤቶች ትዕዛዝ አለመከበር እጅግ አሳሳቢ ነው” ያሉት ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) ሁኔታው “አፋጣኝ ትኩረትና እልባት” የሚሻ ነው ማለታቸውን ከኮሚሽኑ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።