ኢሰመኮ፤ የአውሮፓ ህብረት ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ስጋቱን ገለፀ
ኮሚሽኑ የውሳኔ ሃሳቡ “እንደ ኢሰመኮ ያሉ ገለልተኛ ተቋማትን ስራ መና የሚያስቀር ነው” ነው ብሏል
ኢሰመኮ፤ ተመድ ለጋራ ምርመራው ምክረ ሃሳቦችና ገለልተኛ ምርመራዎች ድጋፍ እንዲሰጥም ጠይቋል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የአውሮፓ ህብረት ባቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ስጋት እንዳለው አስታወቀ።
ኮሚሽኑ፤ የአውሮፓ ህብረት ባቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ያለውን ስጋት ለተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ናዝሃት ካን፣ ለምክር ቤቱ አባል ሀገራት እንዲሁም ለተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባቸሌት በድብዳቤ አስታውቋል።
በሰሜን ኢትዮጵያ ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ እየደረሰ ያለው የሰብአዊ መብት ጥሰትና እንዳሳዘነው የገለጸው ኮሚሽኑ፤ አውሮፓ ሕብረት የውሳኔ ሀሳብ በሺዎች የሚቆጠሩ ተጎጂዎችን መብት ለማስከበር የተጀመሩ አወንታዊ ሂደቶችን የሚቃረን ነው ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ ከጋራ የምርመራ ቡድኑ ጋር ተመሳሳይ ሚና ያለው አካል ለማቋቋም የቀረበው ሀሳብ ሌላው ስጋት ውስጥ የከተተው ውሳኔ ሃሳብ እንደሆነ ኮሚሽኑ አስታውቋል።
በተጨማሪም “የውሳኔ ሃሳቡ የወንጀል ምርመራ እና ክስ ሂደትን ሊያዘገይ ይችላል ፤ በጋራ ምርመራው ምክረ ሃሳብ መሰረት በመንግስት የሚወሰዱ እርምጃዎችን ሊያቆም ይችላል፤ ተጠያቂዎች ሪፖርቱን ውድቅ ለማድረግ አማራጭ ይሰጣል፤ እንዲሁም እንደ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ያሉ ገለልተኛ የሰብአዊ መብት ተቋማትን ስራ እና ድምጽ የሚንድ ነው” ሲል ኢሰመኮ ያለውን ስጋት አስቀምጧል።
በውሳኔ ሃሳቡ ላይ ያለውን ስጋት የገለጸው ኢሰመኮ፤የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የጋራ ምርመራ ምክረ ሃሳቦች ተግባራዊ እንዲሆኑ ድጋፍ እንዲሰጥ እና ገለልተኛ ምርመራዎችን እንዲያበረታታም ጠይቋል።
ኢሰመኮ፤ ሁሉም በግጭቱ ውስጥ ያሉ አካላት በተለይም የኤርትራ መንግስት እና ህወሓት ኃላፊነታቸውን አምነው በጋራ የምርመራ ሪፖርቱ የቀረቡትን ሃሳቦች ሳይዘገዩ ተግባራዊ ለማድረግ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቋል።
ከዚህ ባለፈም የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቢሮ/OHCHR/እና ኢሰመኮ የጀመሩትን የጋራ ምርመራ ከተቋረጠበት ቀን ሰኔ 28 ቀን 2021 በኋላ፤ ሊደረስባቸው በማይችልባቸው አካባቢዎች የተፈጸሙ ጥሰቶች እና የመብት ጥሰቶች ላይ ተጨማሪ የጋራ ገለልተኛ ምርመራ እንዲቀጥል የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እንዲደግፍም ምክር አቅርቧል።
የኢሰመኮ የጋራ የምርመራ ቡድን እና የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽ/ት ቤት፤ ከህዳር 3 ቀን 2020 እስከ ሰኔ 28 ቀን 2021 በነበሩት ጊዜያት በትግራይ በጦርነቱ ተዋናዮች ሳይፈጸሙ እንዳልቀሩ የሚነገርላቸውንና የዓለም አቀፍ የሰብአዊ ህግጋትን የጣሱ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ የጋራ ምርመራ ማካሄዱ አይዘነጋም።
የጋራ ምርመራው ተልዕኮ በትግራይ ስላለው የሰብአዊ መብት አያያዝ የስርዓተ-የፆታ ሁኔታን ጨምሮ ከባድ የተባሉ ጥሰቶችን መለየት ነበር ያለው ኮሚሽኑ፤የተካሄደው የጋራ የምርመራ የተሟላ ዘገባ ነው ባይባልም፣ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የተፈጸሙ ጥሰቶችን እና የመብት ጥሰቶችን ዋና ዋና ዓይነቶች እና አጠቃላይ ዘይቤዎችን በትክክል ያሳየ ነው ብሏል።