የትግራይ ግጭት ተሳታፊዎች “በተለያየ መጠን” የሰብአዊ መብቶችን መጣሳቸውን የምርመራ ቡድኑ ገለፀ
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና የተመድ የሰብዓዊ መብት ቢሮ በትግራይ ግጭት ዙሪያ ያደረጉት የጋራ ምርመራ ሪፖርት ይፋ ሆነ
በጦር ወንጀለኝነት ጭምር ሊያስጠይቁ የሚችሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ጥፋቶቹ ዘር የማጥፋት አይደሉም
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ቢሮ በትግራይ ግጭት ዙሪያ ያደረጉትን የጋራ ምርመራ ሪፖርት ዛሬ ይፋ አድርገዋል።
በሪፖርታቸውም በግጭቱ ተሳታፊ አካላት መጠኑ ቢለያይም የሰብአዊ መብት እና ዓለም አቀፍ የስደተኞች መብት ጥሰቶችን ጨምሮ እስከ ጦር ወንጀል ሊደርሱ የሚችሉ ጥሰቶችን መፈፀማቸውን አስታውቀዋል።
በጋራ ሪፖርቱ በግጭቱ ተሳትፈው የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል ያላቸው አካላትም፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት፣ የትግራይ ልዩ ሀይል እና ሚሊሻ እንዲሁም የአማራ ልዩ ሀይል እና ሚሰሻዎች መሆናቸውንም አመላክቷል
ሪፖርቱ ከጥቅምት 24 2013 ዓ.ም እስከ ሰኔ 21 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ንጹሃንና ማጥቃት፣ የንጹሃንን ንብረት ማጥቃት፣ ከህግ ውጭ የሆነ ግድያ፣ ማሰቃየት እና ማገት፣ ህገ ወጥ የሆነ እስር፣ ጾታዊ እና ሌሎችም የሰብዓዊ መብት ጥሰጥ ጥቃቶች መፈጸማቻን ጠቅሷል።
ከዚህ በተጨማሪም በትግራይ ክልል በሚገኙ የስተደኛ ጣቢያዎች ላይ በፈረንጆቹ ከህዳር 2020 እስከ ጥር 2021 ድረስ የተለያዩ ጥቃቶች መፈፀማቸውን ያስታወቀው ሪፖርቱ፤ የትግራይ ሀይሎች በስደተኛ ጣቢያ የሚገኙ የስደተኞችን ንብረት እና የተመድ ንብረቶችን መዝረፋቸውን አስታውቋል።
በዚህም በፈረንጆቹ ጥቅምት 28፤ 2020 የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከያዘው ተራራማ ስፍራ በተተኮሰ ከባድ መሳሪያ 15 የሲቪሎች ንብረቶች ላይ በማረፍ 29 ሰዎችን መገደላቸውን እና 34 ሰዎች መቁሰላቸውን ሪፖርቱ አመላክቷል።
በፈረንጆቹ ከህዳር 9 እስከ 11፤ 2020 በሁመራ በተካሄደ ከባድ ውጊያ ከኤርትራ መካላከያ ሰራዊት እና ከትግራይ ልዩ ሀይል በተተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች 15 ሰዎች መሞታቸውን እና በርካቶች መቁሰላቸውን በሪፖርቱ ተካቷል።
ከህግ ውጭ የሆነ ግድያ በፈረንጆቹ ከህዳር 9 እስከ 10 2020 “ሳምሪ” በመባል የሚጠራ የትግራይ ወጣቶች ቡድን በማይካድራ ከ200 በላይ የአማራ ተወላጆችን መግደላቸውን ያመላከተው ሪፖርቱ፤ በስፍራው የበቀል ግድያዎች በትግራይ ተወላጆ ላይ መፈፀማቸውንም አስታውቋል።
በፈረንጆቹ ህዳር 28፤ 2020 የኤርትራ መከላከያ ሰራዊት በአክሱም ከተማ ከ100 በላይ ወጣቶችን መግደሉም በሪፖርቱ የተመላከተ ሲሆን፤ በግጭቶ ቀጥተኛ ተሳትፎ የሌላቸው ሰዎች መገደላቸው የጦር ወንጀል ተፈጽሞ ሊሆን እንደሚችል በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በግጭቱ ምናልባትም የዘር ማጥፋት ወንጀሎች ተፈጽመው ይሆን ወይ የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የምርመራ ቡድን አባላቱ በሪፖርታቸው ያን አለማረጋገጣቸውን ገልጸዋል፡፡
የገጠሙ ችግሮችን በተመለከተ ሰላባዎችን፣ ጠይቀናል ሆኖም ስለዘር ማጥፋቱ ያረጋገጥነው ነገር የለም በሪፖርታችንም አልተጠቀሰም ሲሉም ነው ያስቀመጡት።
ዋና ኮሚሽነር ዳንዔል በቀለ በበኩላቸው ምርመራው በጦር ወንጀለኝነት ጭምር ሊያስጠይቁ የሚችሉ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን ማረጋገጡን በመጠቆም ነገር ግን ጥፋቶቹ ዘር የማጥፋት አይደሉም ሲሉ ተናግረዋል።