በግጭቱ በጦር ወንጀለኝነት ጭምር ሊያስጠይቁ የሚችሉ ወንጀሎች ቢፈጸሙም ጄኖሳይድ መፈጸሙን ግን ለማረጋገጥ አልተቻለም ተብሏል
በትግራዩ ግጭት ዘር የማጥፋት ወንጀል (ጄኖሳይድ) መፈጸሙን የሚያመለክቱ ማስረጃዎች አለመገኘታቸው ተገለጸ፡፡
በግጭቱ በጦር ወንጀለኝነት ጭምር ሊያስጠይቁ የሚችሉ ወንጀሎች መፈጸማቸውን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን አግኝቻለሁ ያለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተመድ ጣምራ የምርመራ ቡድን ዘር የማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን የሚያረጋግጡ ማስረጃዎችን ግን አላገኘሁም ብሏል፡፡
የምርመራ ሪፖርቱን ዛሬ ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ/ም ይፋ ያደረገው ጣምራ ቡድኑ “የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ሰላባዎችን ጠይቀን በሪፖርታችን አካተናል፤ ሆኖም ስለ ዘር ማጥፋቱ ያረጋገጥነው ነገር የለም፤ ይህም በሪፖርታችን አልተካተተም” ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በምርመራ ሪፖርቱ የተወሰኑ ይዘቶች ላይ ትልቅ ቅሬታ እንዳለው ገለጸ
በምርመራው በጦር ወንጀለኝነት ጭምር ሊያስጠይቁ የሚችሉ ሰፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን መረጋገጡን የተናገሩት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ዳንዔል በቀለ (ዶ/ር) በበኩላቸው “ጥሰቶቹ ዘር የማጥፋት አይደሉም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር ዳንዔል በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ (ክራይም አጌንስት ሂዩማኒቲ) እና በጦር ወንጀለኝነት ሊያስጠይቁ የሚችሉ ሁለት የወንጀል ዐይነቶች ተፈጽመዋል ብለን እናምናለን፤ ይህንንም በምርመራችን አረጋግጠናል ብለዋል፡፡
“የተጨማሪ ምርመራ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ቡድኑ በጣምራ በሰበሰበውና በተነተነው መረጃ መሰረት የወንጀሎቹ ዐይነት በሰብዓዊነት ላይ የተፈጸሙ እና በጦር ወንጀለኝነት ሊያስጠይቁ የሚችሉ ሊሆኑ ይችላሉ ስንል ነው ድምዳሜ ላይ የደረስነው”ሲሉም ኮሚሽነሩ አክለዋል፡፡
የምርመራ ሪፖርቱ ግኝቶች ጄኖሳይድ መፈጸሙን አለማመልከታቸውንም ነው የጠቆሙት፡፡
የማይካድራው ጭፍጨፋ በርካታ ንፁሃን የተገደሉበት ዓለም አቀፍ የሽብር ወንጀል ሆኖ ተመዘገበ
ከሰብዓዊ እርዳታዎች ጋር በተያያዘ “መንግስት ርሃብን እንደ ጦር መሳሪያ ተጠቅሟል” በሚል የሚቀርቡ ክሶችን በተመለከተ የተጠየቁት ዶ/ር ዳንዔል “ክሶቹን በምርመራችን ለማረጋገጥ አልቻልንም” ሲሉ መልሰዋል፡፡
በጣምራ የቀረበው ሪፖርት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ/ም የትግራይ ኃይሎች መቀሌ ይገኝ በነበረው ሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውንን ተከትሎ መንግስት የአጸፋ እርምጃዎች መውሰዱን አመልክቷል፡፡
‘ሳምሪ’ የተባለው የትግራይ ወጣቶች ቡድን በማይካድራ በፈጸመው ግድያ ከ200 የሚበልጡ ንጹሃን አማራዎች መገደላቸውንም ነው ሪፖርቱ ያስቀመጠው፡፡
ሆኖም ኮሚሽኑ ኅዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም አውጥቶት በነበረው የመጀመሪያ ደረጃ ቀዳሚ ሪፖርት በማይካድራ እና በአካባቢው በተፈጸመው ጭፍጨፋ ከ600 የሚልቁ ንጹሃን መገደላቸውን በመግለጽ ቁጥሩ ሊጨምር ሆነ ሊቀንስ እንደሚችል ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡