የኦሮሚያ ክልል “የኢሰመኮ መግለጫዎች ሚዛናዊነትን ያልጠበቁ ናቸው” ሲል ተቸ
ኮሚሽኑ የሚያወጣቸው መግለጫዎች “በኦሮሚያ ክልል ብቻ ላይ ያተኮሩ ናቸው” ሲልም ክልሉ ቅሬታ አሰምቷል
ኮሚሽኑ “ከስህተቶቹ ሊታረም” እና ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በትብብር ሊሰራ እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልለ አስታውቋል
የኦሮሚያ ክልል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ክልሉን አስመልክቶ የሚያወጣቸው መግለጫዎች “ሚዛናዊነተትን ያልጠበቁ ናቸው” ሲል ተቸ።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ እና የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ኃላፊ አቶ ሁሴን ዑስማን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ፣ በወቅቱ ከተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች፣ በወቅቱ በተፈጸሙ ሰብአዊ ቀውሶችና በሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ በሚያወጣቸው መግለጫዎች ዙሪያ ለጋዜጠኞች መግለጫ መስጠታቸውን ኦ.ቢ.ኤን ዘግቧል።
የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ በመግለጫው “የዜጎችን ሰብአዊ መብት ማስከበር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን የመላው ዜጎች፣ የጸጥታ አካላትና የፍትህ ተቋማት ጭምር ነው” ብለዋል።
የጸጥታ አካላት፣ የፍትህ ተቋማትና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ለዜጎች ሰብዓዊ መብት መከበር እርስ በርስ ተቀናጅተው የሚሰሩ አካላት እንጂ የሚካሰሱ ተቋማት እንዳልሆኑም ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ጋር ተያይዞ ከ10 ወራት በፊት ኮሚሽኑ ባወጣው ሪፖርት “ፖሊስ የጸጥታ ችግሩን ለመቆጣጠር ግዳጁን አልተወጣም ፤ ሕይወት እና ንብረትን ከጥፋት መታደግ አልቻለም ፤ በወቅቱ የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር ለመቆጣጠር ፖሊስ ተመጣጣኝ እርምጃ አልወሰደም ፤ በሕግ ማስከበር ወቅቱ የዜጎች ህይወት ጠፍቷል” የሚሉ ቅሬታዎች መቅረባቸውን ኃላፊዎቹ ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ከ11 ወራት በኋላም በዚሁ በአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያና በወቅቱ በተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ዙሪያ ያወጣው መግለጫም ከበፊቱ መግለጫ ጋር ቅርበትና ተመሳሳይነት ያለው ከመሆኑም በላይ የኦሮሚያ ፖሊስ የወሰዳቸውን የማስተካከያ እርምጃዎች በአግባቡ ያላካተተ ሪፖርት መሆኑንም ገልጸዋል።
“የክልሉ ፖሊስ፣ የክልሉ ዐቃቤ ሕግ፣ የጸጥና የፍትህ አካላት ኮሚሽኑ በተለያዩ ጊዜያት የሚያነሳቸውን ቅሬታዎች አጣርተው እርምጃ በመውሰድ ላይ ይገኛሉ፤ እየወሰደ ያለው እርምጃም ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉም ተናግረዋል።
“ይሁን እንጂ ኮሚሽኑ አብዛኛውን ጊዜ የሚያወጣቸው መግለጫዎች በኦሮሚያ ክልል ብቻ ላይ ያተኮሩና ኦሮሚያን ብቻ ማዕከል ያደረጉ ናቸው” በማለት ኃላፊዎቹ ቅሬታቸውንም አሰምተዋል።
“አብዛኛው ሪፖርቶች ጥቂት ግለሰቦችና የተወሰኑ ወገኖች በሚያቀርቡት ቅሬታ ላይ የተመሠረቱ ናቸው ፤ መግለጫዎቹም ሚዛናዊነቱን የጠበቁ አይደሉም” ብለዋል።
“ኮሚሽኑ ወገንተኛና ሚዛናዊነቱን ያልጠበቀ መረጃ ይዞ መንግስትንና የጸጥታ አካላትን ከመውቀስ ውጭ ሕወሓት እና ሸኔ በንጹሐን ዜጎች ላይ እየፈጸሙ ስላሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ትኩረት ሰጥቶ መናገር አይፈልግም” ሲሉም ኢሰመኮን ተችተዋል።
“ስለ ጽንፈኞች ሃገር አፍራሽነት ሪፖርት የማቅረብ ፍላጎትም የለውም፤ የሚወጡት መግለጫዎችም አብዛኛውን ጊዜ ለጸረ ሰላም ሐይሎች ሽፋን የሚሰጥ ነው” ብለዋል።
“በመግለጫ ጋጋታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ማስቀረት ስለማይቻል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሚዛናዊ ያልሆኑ መግለጫዎችን ከማውጣት ሊቆጠብ ይገባል፤ ከስህተቶቹም ሊታረምና ከሌሎች ባለ ድርሻ አካላት ጋር በትብብር ሊሰራ ይገባል” ሲሉም ነው የገለጹት።
“የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ከአላስፈላጊ የብሔርና የፖለቲካ ወገንተኝነትና ጥገኝነት ነጻ በመሆን ለሰብአዊ መብቶች መከበር ብቻ ሊቆም እንደሚገባም” አሳስበዋል።