“በኦሮሚያ አሁንም ንብረታችሁን እናቃጥላለን ፤ እንገላችኋለን የሚል ማስፈራሪያ አለ”-ኢሰመኮ
ተጎጂዎችን ወደ ቤታቸው ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ዝቅተኛ ነው ብሏል ኢሰመኮ
ኢሰመኮ መንግስት የጥቃት ማስፈራሪያዎችንና ዛቻዎችን በመመርመር እንዲከላከል መክሯል
ኢሰመኮ መንግስት የጥቃት ማስፈራሪያዎችንና ዛቻዎችን በመመርመር እንዲከላከል መክሯል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በአሮሚያ ክልል አሁን ላይ የተሻለ መረጋጋት ያለ ቢሆንም በአንዳንድ አካባቢዎች በሰዎች ህይወት፣ ደህንነት እና ንብረት ላይ የጥቃት ስጋት መኖሩን ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
ኮሚሽኑ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የተከሰተውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለማጣራት ችግሩ ተከስቶባቸዋል በተባሉ ከ40 በላይ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች ላይ የምርመራ ቡድኖችን አሰማርቷል፡፡
ኮሚሽኑ በመግለጫው በአንዳንድ አካባቢዎች የሚገኙ ተጎጂዎች እና ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያዩ ቡድኖች የጥቃት ማስፈራሪያ እና ዛቻ እየደረሳቸው እንደሆነ ገልጿል፡፡ ለአብነትም በዶዶላ ከተማ የሚገኙ የጉዳቱ ተጠቂዎች ከግጭቱ በኋላ ማለትም ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም ከ60 ሰዎች በላይ ስማቸውን በመዘርዘር ከተማውን ለቀው ካልወጡ እርምጃ የሚወሰድባቸው መሆኑን የሚገልጽ ማስጠንቀቂያ ያዘለ ወረቀት መሰራጨቱን ኮሚሽኑ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
በባቱ ከተማ ተጎጂዎች አሁንም ከተማውን ለቀው እንዲወጡ በስልክና አካል ማስፋራሪያ እየደረሳቸው መሆኑን እና ሻሸመኔ ከተማ ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች ቤት ለቤት እየሄዱ ከ5 እስከ 10 ሺህ ብር ካላመጣችሁ አሁንም ንብረታችሁን እናቃጥላለን እንዲሁም እንገላችኋለን በማለት ማስፈራሪያ እየደረሳቸው መሆኑንም ነው ኮሚሽኑ ይፋ ያደረገው፡፡
በተወሰኑ አካባቢዎች በመንግስት የፀጥታ አካላት ሳይቀር ሰዎች እየተደበደቡና ዛቻ እየተፈፀመባቸው መሆኑን ገልጾ ይህም በቡራዩ ከተማ ከታ እና በጉና ወረዳ ነገሌ ከተማ መደረጉን አስፍሯል፡፡
ኢሰመኮ በተፈጠረው ችግር ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ከጉዳታቸው ሳያገግሙ ለሌላ ጥቃት እንዳይዳረጉ መንግስት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት አሳስቧል፡፡
የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልል መንግስታት የአስተዳደር እና የፀጥታ አካላት ከላይ በተጠቀሱት ስፍራዎች የደረሱ ማስፈራሪያዎች እና ዛቻዎችን በፍጥነት በመመርመር የመከላከል እና አጥፊዎችን የመቆጣጠር ስራ እንዲሰሩም ጠይቋል፡፡
የሕግ አስከባሪ እና የፀጥታ አካላት ኃላፊነታቸውን በሚወጡበት ወቅት የሰዎችን ሰብዓዊ መብቶች በማክበር እንዲንቀሳቀሱ ቁጥጥር በማድረግ እና ችግሮች በተከሰቱባቸው ቦታዎችም በፍጥነት የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ እና ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ እንዲሰሩም አሳስቧል፡፡ የፀጥታ ስጋት ይኖርባቸዋል ተብለው የሚታሰቡ ሌሎች ስፍራዎችን በመለየት ተጨማሪ ጥበቃ እንዲደረግም ኮሚሽኑ ምክረ ሀሳብ አቅርቧል፡፡
ተጎጂዎቹ ለዕለቱ በህይወት ለመቆየት የሚያስፈልጋቸውን ሰብዓዊ እና ሌሎች ድጋፎችን ማቅረብ እንደሚገባና ተፈናቅለው ለሚገኙ ዜጎች ተገቢውን ጥበቃ ማድረግ እንድሁም ቤታቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት አፋጣኝ ሥራ ነውም ብሏል ኮሚሽኑ፡፡ በተለይም የመኖሪያ ቤታቸው እና ንብረታቸው የወደመባቸው ተጎጂዎች አሁንም በሰው ቤት፣ በኃይማኖት ተቋማት እና በሌሎች ስፍራዎች ተጠልለው የሚገኙ ዜጎችን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ የሚደረገው ጥረት ዝቅተኛ መሆኑንም ኮሚሽኑ ይፋ አድርጓል፡፡
በተወሰኑ አካባቢዎች በተለይም በአብያተ ክርስትያናትና በሌሎች ቦታዎች የተጠለሉ ሰዎች ለደህንነታቸው ማረጋገጫ ሳይሰጥ የመንግስት ኃላፊዎች ወደ ዜጎቹን ወደ ቤታችሁ ካልተመለሳችሁ እርዳታ አታገኙም የሚል አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ እየተጫነባቸው መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ ይህ በተለየ ሁኔታ በሻሸመኔ እና አጋርፋ እንደተስተዋለና ተገቢ እንዳልሆነም ነው ገልጿል፡፡
የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስታት ከቤታቸው የተፈናቀሉ ሰዎችን ዝርዝር መረጃ በማጠናከር፣ ተገቢውን ጥበቃ እና አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ በማድረግ በፍጥነት ወደ ቤታቸው እንዲመለሱም ኮሚሽኑ ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
በእስር ላይ የሚገኙ ሰዎችን በተመለከተ እስከ አሁን ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ታሳሪዎችን በአፋጣኝ ወደ ፍርድ ቤት ማቅረብ እና የዋስትና መብት የተረጋገጠላቸውን እስረኞች ዋስትናውን አክብሮ ከእስር መልቀቅ እንደሚገባ ኢሰመኮ ገልጿል፡፡
ኢሰመኮ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተከሰተው የሰላም መደፍረስ ምክንያት የተከሰተውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ከሰብዓዊ መብት መርሆዎች አንፃር በመተንተን ዝርዝር የምርመራውን ግኝቶች እና የመፍትሄ ሀሳቦች በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚያሳውቅ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡