በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ከ100 ባለይ ሲቪል ሰዎች በታጣቂዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ ገለፀ
ጥቃቱ “በኦነግ ሸኔ፣ በአማራ ኢመደበኛ ታጣቂ ኃይሎችና ግለሰቦች በተከታታይ መፈጸሙን” ኢሰመኮ አስታውቋል
መንግስት “ከሰሞኑ ሸኔ በሆሮ ጉድሩ ወለጋ በንጹሐንና ዜጎችና በአካባቢው ሚሊሻ አባላት ላይ ግድያ ፈጽሟል” ብሏል
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን፤ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በታጠቁ ቡድኖች በሲቪል ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች መቀጠላቸው እጅግ አሳሳቢ ነው” አለ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ይህን ያለው ጳጉሜ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል፣ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ኡሙሩወረዳ በሲቪል ሰዎች ላይ የደረሰን ግድያ አስመልክቶ ትናንት ባወጣው መግለጫ ነው።
በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በኡሙሩ፣ በሆሮ ቡልቅ እና በጃርደጋ ጃርቴ ወረዳዎች ከነሐሴ 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት 3 ሳምንታትውስጥ ብቻ በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ)፣ በአማራ ኢመደበኛ ታጣቂ ኃይሎች እና ግለሰቦች በተከታታይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ100 በላይ ሲቪል ሰዎች መገዳለቻወም አስታውቋል።
በሰዎች ግድያ በተጨማሪ የግል ንብረት እና የቁም ከብቶች መዘረፋቸውን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎችም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው ያለበቂ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ የሚገኙ መሆኑን ኮሚሽኑ ከተጎጂ ቤተሰቦች፣ ከአካባቢው የፍትሕና የአስተዳደር አካላት እንዲሁም በአካባቢው ከሚንቀሳቀሱ የእርዳታ ድርጅቶች ካሰባሰባቸው መረጃዎች እና ማስረጃዎች ማረጋገጡን ገልጿል።
በዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች ተጨማሪ የጸጥታ ስጋቶች በመኖራቸው በታጠቁ ቡድኖች በሲቪል ሰዎች ላይ ብሄርን መሰረት ያደረጉ ተጨማሪ ጥቃቶች እንዳይፈጸሙ ለመከላከል በትኩረት እንዲሰራም መግለጫው አመላክቷል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ መንግስት የሲቪል ሰዎችን ደህንነት የማስጠበቅ ግዴታውን በአግባቡ መወጣት ይኖርበታል ሲሉ አሳስበዋል።
“የክልሉ እና የፌዴራል መንግስት በአካባቢው ብሔርን መሰረት አድርገው የሚፈጸሙ ጥቃቶችን ለመከላከል በመወሰድ ላይ የሚገኙትን እርምጃ ችግሩን በሚመጥን ደረጃ በማሳደግ የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል”ም ነው ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ።
ከኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባሳለፍነው ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ “ከሰሞኑ ሸኔ ሆሮጉድሩ ወለጋ በንጹሐንና ዜጎችና በአካባቢው ሚሊሻ አባላት ላይ ግድያ ፈጽሟል” ብሏል።
“አሸባሪው ሸኔ ይሄንን ግድያ በንጹሐን ላይ የወሰደው በሁለት ምክንያቶች መሆኑ ታውቋል” ያለው መንግስት፤ የመጀመሪያው “የተደመሰሱበትን ጃል ኡርጂ የተባለውን የአካባቢውን የሸኔ አዛዥና ጀሌዎቹን ደም ለመበቀል ነው” ብሏል።
“በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው የሚገኙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው አካባቢውን ከአሸባሪው ሸኔ በማፅዳት ላይ ይገኛሉ” ሲልም መንግስት በመግለጫው አስታውቋል።