ነዋሪዎቹ ንጹሃን በማንነታቸው ምክንያት እየተገደሉ መሆኑ ገልጸዋል
በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉድሩ ወለጋ ዞን ንጹሃን በማንነታቸው ምክንያት እየተገደሉ መሆናቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጹ፡፡
ነዋሪዎቹ ለአል ዐይን አማርኛ እንደገለጹት ግድያው ማንነት ላይ ያነጣጠረ ነው፡፡
“ዜጎች አማራ በመሆናቸው ብቻ እየተገደሉ ነው” ያሉት ለደህንነታቸው በመስጋታቸው ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የአካባቢው ነዋሪዎች የኦሮሚያ ልዩ ኃይል እና የፌዴራል ፖሊስ በስፍራው መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡
ሆኖም ከዚህ ይልቅ “የሀገር መከላከያ ሰራዊት ወደ ስፍራው እንዲገባ እንፈልጋለን ነው” ነዋሪዎቹ ያሉት፡፡
ከሰሞኑ በዞኑ በአቤ ደንጎሮ ወረዳ ቱሉ ገና ቀበሌ በርካታ ሰዎች በማንነታቸው ተለይተው መገደላቸው ተነግሯል፡፡
ከአንድ ቤተሰብ አምስት ሰዎች “መታረዳቸውን”ም ነው ሁኔታውን ተመልክተናል ያሉት ነዋሪዎቹ ለአል ዐይን የተናገሩት፡፡
አል ዐይን ማንነትን መሰረት አድርጎ ተፈጽሟል የተባለውን ይህን የንጹሃን ግድያ በተመለከተ የክልሉን ፖሊስ ኮሚሽነር እና የክልሉን ቃል አቀባይ ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት የእጅ ስልካቸውን ባለማንሳታቸው ምክንያት አልተሳካም፡፡
ከዚህ በፊት በተመሳሳይ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን የክልሉ የመንግስት መግለጹ ይታወሳል፡፡