ከምዕራብ ወለጋ ተፈናቅለው ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰፈሩ ተፈናቃዮች ድጋፍ ቆሞብናል አሉ
ክልሉ በምእራብ ወለጋ ያለው የጸጥታ ችግር እርዳታውን አስተጓጉሏል ብሏል
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በባምባሴ መጠለያ ጣቢያ ያሉት ተፈናቃዮች አሁን ላይ ድጋፍ እየደረሳቸው አይደለም ሲል የነዋሪዎቹን ቅሬታ አረጋግጠዋል
ባለፈው ህዳር 8 እና 9፤2014 ዓ.ም ከኦሮሚያ ክልል ከምዕራብ ወለጋ ተፈናቅለው በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሰፈሩ ተፈናቃዮች ድጋፍ አልደረሰንም ሲሉ ተናገሩ፡፡
ከምዕራብ ወለጋ ከባቦ ጋምቤል ወረዳ የተለያዩ ቀበሌዎች ተፈናቅለው በቤንሻብጉል ጉሙዝ ክልል በሚገኘው በባምባሴ ወረዳ የሚገኙት ተፈናቃዮች ከሚያዚያ 29 ቀን 2014 ዓ.ም ወዲህ ምንም ድጋፍ እንዳልደረሳቸው ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ተፈናቃዮቹ ድጋፍ እንዲደረግላቸው በመጠየቅ ላይ ናቸው፡፡
በባምባሴ ወረዳ በሁለት መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙት እነዚህ ተፈናቃዮች ከቤታቸው የወጡት ሕዳር 8 እና 9 ቀን ሲሆን ወደ መጠለያ ጣቢያዎቹ የደረሱት ህዳር 12 ቀን 2014 መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አሁን ላይ ባምባሴ በሚገኘው ኳስ መጫወቻ ሜዳ ውስጥ ከሚገኙት ተፈናቃዮች መካከል ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የ 51 ዓመት ጎልማሳ የተፈናቃዮቹ ተወካይ ናቸው፡፡ ጎልማሰው እንደሚሉት ሕዳር፣ ጥር አና ሚያዚያ ላይ ድጋፍ ሲደረግላቸው ቢቆይም፤ ከሚያዚያ ወዲህ ባሉት ወራት ግን ምንም ድጋፍ እንዳልደረሳቸው ነው የገለጹት፡፡
ሌላዋ ስማቸው እንዳይጠቀስ የገለጹትና ሕጻን ልጅ ይዘው የተሰደዱት ወ/ሮ ፤ የገጠማቸውን ችግር ለመገናኛ ብዙኃን እንዳይናገሩ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡ ከሚያዚያ ጀምሮ እስካሁን ድጋፍ እንዳላገኙ ያነሱት እመጫቷ የሚበላ ነገር ለመግዛት ገንዘብ ስለሌላቸው መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ መጠለያ ጣቢያ ውስጥ የገጠማቸውን ችግር ለመገናኛ ብዙሃን እንዳትናገሩ መባላቸው ያነሱት ተፈናቃይ አሁን ያለው ችግር እጅግ የከፋ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሽ ዞን በሎ ጀገንፎይ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮችም ከግንቦት ጀምሮ አቤቱታ እያቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በክልሉ በተለያዩ ቦታዎች የተፈናቃዮች ጣቢያዎች መኖራቸው የሚታወቅ ሲሆን ዕርዳታ እየደረሰ አለመሆኑ በተደጋጋሚ ይደመጣል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አቶ ታረቀኝ ቴሲሳ በባምባሴ ወረዳ መጠለያ ያሉት ተፈናቃዮች 13 ሺ መሆናቸውንና በትክክልም አሁን ላይ ድጋፍ እንዳልደረሳቸው ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ፤ መንግስት ድጋፍ ለማድረግ የአቅርቦት ችግር እንደሌለበት አንስተው በባምባሴ ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚሆን ድጋፍ በጉዞ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ አቶ ታረቀኝ ድጋፉ ለተፈናቃዮች እንዳይደርስ እንቅፋት የሆነው እርዳታ በሚጓጓዝበት በምዕራብ ወለጋ ያለው የጸጥታ ችግር እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጭ ለመጡ ተፈናቃዮች ምግብ ነክ እና ምግብ ነክ ያልሆነ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን ያነሱት አቶ ታረቀኝ በመንገድ ያለው የጸጥታ ችግር ግን እንቅፋት ነው ብለዋል፡፡
ምግብ ነክ ያልሆኑት ድጋፎች ላይ አሁን ምንም ችግር እንደሌለ የገለጹት አቶ ታረቀኝ፤ የምዕራብ ወለጋ መንገድ በመዘጋቱ የምግብ ነክ ድጋፍ ማድረስ አለመቻሉን አንስተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ባምባሴ ላሉት ብቻ ሳይሆን ሸርቆሌና ሌሎች ቦታዎች ላሉ ተፈናቃዮች ድጋፍ ማድረስ እንዳልተቻለ ነው የተናገሩት፡፡
በምዕራብ ወለጋ ድጋፍ የሚመጣላቸው ተፈናቃዮች በአካባቢው አለመረጋጋት ምክንያት ድጋፉን አለማግኘታቸውን አቶ ታረቀኝ አስታውቀዋል፡፡ ለተፈናቃዮች ድጋፍ የጫኑ 10 ተሳቢዎች ጊምቢ ላይ ከቆሙ 31ኛ ቀናቸው እንደሆነም የሥራ ኃላፊው አቶ ታረቀኝ የተናገሩት፡፡
የጸጥታ ኃይሎች አሁን ተልዕኮ ላይ እንደሆኑ ያነሱት ሃላፊው የመንገዱ ሁኔታ ሲስተካከል ድጋፉ በቀጥታ ከተፈናቃዮች እንደሚደርስ አቶ ታረቀኝ ቢገልጹም በባምባሴ የሚገኙ ተፈናቃዮች ግን ችግሩ የመንገድ ብቻ ሳይሆን በትክክል የማድረስ ችግር እንደሆነ ያነሳሉ፡፡ አቶ ታረቀኝ ይህንን ጉዳይ ፖለቲካ ለማድረግ የሚሰሩ እንዳሉ ቢገልጹም እነማን ናቸው ለሚለው ግን ምላሽ አልሰጡም፡፡