በህገ ወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመገባት የሞከሩ ኢትዮጵያዊያን ጉዳት ደረሰባቸው
ኢትዮጵያዊያኑን የጫነ ተሸከርካሪ በዛምቢያ ውስጥ ከፍጥነት በላይ ሲያሽከረክር አደጋ አጋጥሞታል ተብሏል
በአደጋው ስድስት ኢትዮጵያዊያን ተጎድተው ሆስፒታል እንደገቡ ተገልጿል
በህገ ወጥ መንገድ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመገባት የሞከሩ ኢትዮጵያዊያን ጉዳት ደረሰባቸው፡፡
ዛምቢያ ህገወጥ ስደተኞች ከምስራቅ አፍሪካ ወደ ደቡብ አፍሪካ ለመግባት የሚተላለፉባት ሀገር ስትሆን ኢትዮጵያዊያንም ይህን መስመር ከሚጠቀሙ ሀገራት ዜጎች መካከል ዋነኞቹ ናቸው፡፡
በትናንትናው ዕለትም ከታንዛኒያ ተነስተው ወደ ደቡብ አፍሪካ በህገወጥ መንገድ ለመግባት የሞከሩ ኢትዮጵያዊያን አደጋ እንዳጋጠማቸው ተገልጿል፡፡
አደጋው ያጋጠመው 12 ኢትዮጵያዊያኑን የጫነ ተሸከርካሪ ከፖሊስ ክትትል ለመሰወር በሚል ከፍጥነት በላይ ሲያሽከረክር ነበር ተብሏል፡፡
በዚህ አደጋ ስድስት ኢትዮጵያዊያን አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን አራቱ ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸው በኦሶካ ሆስፒታል የህክምና ክትትል ላይ እንደሆኑ የሀገሪቱ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡
ዛምቢያ ከታንዛኒያ ጋር የምትዋሰንበት ኢሶካ ግዛት ከምስራቅ አፍሪካ የሚነሱ ህገወጥ ስደተኞች ይተላለፉባታል፡፡
ባሳለፍነው ታህሳስ ወር ላይ እድሜያቸው ከ20 እስከ 38 የሚሆናቸው 27 ኢትዮጵያዊያን አስከሬን በዛምቢያ መዲና ሉሳካ ከተማ አቅራቢያ በአንድ ስፍራ ህይወታቸው አልፎ መገኘቱ ይታወሳል፡፡
እንዲሁም ሕዳር ወር ላይ ደግሞ ከ30 በላይ ኢትዮጵያዊያን አስከሬን በማላዊ ልዩ ቦታው ምታንጋታንጋ ተብሎ በሚጠራ ጫካ ውስጥ በአንድ ቦታ ተቀብሮ መገኘቱም አይዘነጋም፡፡
በወቅቱ የኢትዮጵያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ጉዳዮቹን ከሀገራቱ መንግስታት ጋር እየተከታተሉት እንደሆነ ገልጸው የነበረ ቢሆንም እስካሁን ስለ ጉዳዩ የተባለ ነገር የለም፡፡