ሳዑዲ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ጉቦ እየተጠየቁ እንደሆነ ተናገሩ
ወደ ጅንካ በመጓዝ ላይ የነበሩ የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች በታጣቂዎች ስለመታገታቸው መረጃ የለም ተብሏል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ ቅሬታዎችን መሰረት በማድረግ አሰራሩን እንደሚፈትሽ ገልጿል
ከሳኡዲ አረቢያ የሚመለሱ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራችን ለመመለስ ጉቦ እየተጠየቅን ነው አሉ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ካነሷቸው ሀሳቦች መካከል በሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ያሉ ኢትዮጵያውያንን የመመለስ ስራው ስላለበት ሁኔታ፣ የኢትዮጵያ እና ሱዳን ድንበር ጉዳይ፣ በትግራይ ክልል ላሉ ዜጎች እየተደረገ ስላለው የሰብዓዊ ድጋፍ እና ሌሎች የዲፕሎማሲ ስራዎች ዋነኞቹ ነበሩ፡፡
በሳኡዲ አረቢያ ባሉ እስር ቤቶች ህይወታቸውን በአስቸጋሪ ሁኔታ እየመሩ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ስራው መጀመሩ ቢያስደስታቸውም አሰራሩ ግልጸኝነት እንደሚጎድለውና ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ጉቦ እንደሚጠየቁ ለአል ዐይን በስልክ ተናግረዋል፡፡
ቅሬታውን መሰረት በማድረግ ስለጉዳዩ የተጠየቁት አምባሳደር ዲና በሰጡት ምላሽ እስከዛሬ ድረስ ከ15 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል ብለዋል።
ከሳኡዲ አረቢያ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውን እየተመለሱ ያሉት ሪያድ ባለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ፣ የሳኡዲ አረቢያ መንግስት በጋራ በሚሰሩት ስራ መሰረት ነው ያሉት ቃል አቀባዩ ነገር ግን "እንደተባለው ጉቦ እየተጠየቁ እና በዚያ መሰረት የተስተናገዱ ዜጎች ካሉ አሰራራችንን ፈትሸን እናስተካክላለን" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ ኢትጵያውያንን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ዘመቻ ተጀመረ
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው በተጨማሪ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የድንበር ይገባኛል ጥያቄ በአዲስ መልክ በማንሳት ላይ መሆኗ ሲሆን የኢትዮጵያ ሱዳን ድንበር ጉዳይ የሚፈታው በሁለቱ ሀገራት የድንበር ኮሚሽን እና ሌሎች ጉዳዩ በሚመለከታቸው የጋራ ተቋሞት እንጂ በሌላ መንገድ አይደለም ብለዋል።
ነገር ግን የሱዳን መንግስት አስቀድሞ መሬቱ የኔ ነው ወደ ሚለው ፍርድ መግባቱ ተቀባይነት አይኖረውም ጉዳዩን በሰላም መፍታት እንፈልጋለን ማለታቸውን ግን እንደሚቀበሉ የኢትዮጵያም ፍላጎት ጉዳዩን በሰላም እና በድርድር መፍታት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በደቡብ ክልል በአርባ ምንጭ አድርገው ወደ ጅንካ በመጓዝ ላይ ያሉ የውጭ ሀገራት ዜግነት ያላቸው ጎብኚዎች በታጣቂዎች ታግተዋል የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነውና ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ መረጃው ምን ይላል? በሚል ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄም "የውጭ ሀገራት ጎብኚዎች ስለመታገታቸው መረጃ የለኝም" ሲሉ ቃል አቀባዩ ምላሽ ሰጥተዋል።
የፌደራል መንግስት በትግራይ ላሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ያለምንም ገደብ ምግብና መድሃኒትን ጨምሮ መሰረታዊ ድጋች በመግባት ላይ መሆኑንም ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።
ሳዑዲ የመኖሪያ እና የስራ ፈቃድ (ኢቃማ) በትንሹ ከ3 ባልበለጡ ወራት ውስጥ እንዲታደስ ወሰነች
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ባሳለፍነው ሳምንት ለተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በጻፉት ደብዳቤ የኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ ምንድን ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም "ግጭቱን ለማቆም የተለያዩ ጥረቶች እየተደረገ ባለበት እና የተለያዩ አዎንታዊ ለውጦች እየተመዘገበ ባለበት ወቅት ይህ መደረጉ ጸብ አጫሪነት ነው" ሲሉ ቃል አቀባዩ ስለጉዳዩ ባጭሩ ገልጸዋል።