“መጤ ጠል” ጥቃት በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስጋት ውስጥ ከቷቸዋል
በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ጥቃት የሚያደረሰው “ዘመቻ ዱዱላ”’ በመባል የሚታወቀው ኢ-መደበኛ እንቅስቃሴ ነው ተብሏል
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ችግር በጉዳዩ ላይ ከደቡብ አፍሪካ መንግስት ጋር እንወያይበታለን ብሏል
ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በሚገኙ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይ የሚፈጸመው መጤ ጠል ጥቃት እየጨመረ መምጣቱ የተባበሩት መንግስታት በቅርቡ ማስጠንቀቁ ይታወሳል፡፡
በተለይም ከዚህ ቀደም የተፈጸሙ ጥቃቶች በመምራት ስሙ እየጎላ የመጣው “ዘመቻ ዱዱላ” የተባለው እንቅስቃሴ በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ እያደረሰ ለው ጥቃት አሁን ላይ እጅጉን እየተባበሰ እንደመጣ ይገለጻል፡፡
በዚህም ሳቢያ በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ የውጭ ዜጎች ባለቤትነት የተያዙ መኖሪያ ቤቶችና የንግድ ተቋማትን በእሳት የማውደምና ግድያዎች ድረጊቶች እየተፈጸሙ እየተፈጸሙ ነው፡፡
ደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የዚህ ህገ-ወጥ ድርጊት ሰላባ ሆነው ያውቃሉ፡፡
በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትጵያውያን ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገረት በሀገሪቱ በሚስተዋሉ መጤ ጠል እንቅስቃሴዎች ምክንያት የበርካታ ኢትዮጵያውያን ሱቆች ተሰብረው ንብረቶታቸው ተዘርፈዋል፡፡
ኑሮው በደቡብ አፍሪካ ያደረገው አቶ ሃፍተ ገ/ስለሴ ፤ በዘጠኙ የደቡብ አፍሪካ ግዛቶቸ መጤ ጠል የሆኑ በተለይም ሀበሻ ላይ ያነጣጠሩ እንቅስቃሴዎች እንደሚስተዋሉ ለአል-ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወደህ “የሀገሪቱን ስራ የተቆጣጠሩት የውጭ ሀገር ዜጎች ናቸው፡ ስለዚህም ሀገራችን ለቀው መውጣት አለባቸው” የሚል ዓላማ ያነገቡ እንቀስቃዎች ማየት የተለመደ ነው ያለው አቶ ሃፍተ ገ/ስላሴ፤ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ስጋት ውስጥ መሆናቸው አስረድቷል፡፡
በተለይም “የዛሬ ስምንት ወር ማንኛውም ሀበሻ ከጁሃንስበርግ መውጣት አለበት፤ ካልወጣ ግን ንብረቱ ይወረሳል እንዲሁም ህይወቱ ያጣል” የሚሉ ዛቻዎች በትዊተርና በተለያዩ ማህበራዊ የትስስር ገጾች ሲሰራጩ በነበሩበት ወቅት ኢትዮጵያውያኑን እጅጉን ያስጨነቀ አጋጠሚ እንደነበርም በአብነት አንስቷል አቶ ሃፍተ፡፡
የአቶ ሃፍተን ሃሳብ የሚጋራው ሌላው የደቡብ አፍሪካ ነዋሪ የሆነው አቶ ተስፋዬ ገብሬ በበኩሉ “አብዛኛው በህገ-ወጥ መንገድ የገባ ስደተኛ በመሆኑ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ይገኛል” ብሏል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ፡ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ እየተስፋፋ ለመጣው መጤ ጠል እንቅስቃሴ ፤ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚያደርጉት ቅስቀሳ ዋነኛ አጀንዳናቸው በውጭ ዜጎች ላይ ያነጣጣረ መሆኑ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
“ፓርቲዎቹ የሀገሬው ሰው በውጭ ሀገር ዜጎች የተያዙትን ስራዎች መልሰን እንሰጠሃለን የሚል የምርጫ ቅስቀሳ ያደርጋሉ”ም ነው ያሉት፡፡
ለዚህም ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጭምር በውጭ ዜጎች ላይ የሚነዙት የጥላቻ ንግግር ጥቃቶቹ እንዲበረክቱ ማድረጋቸውን ገልጸዋል ኢትዮጵያውያኑ የደቡብ አፍሪካ ነዋሪዎች።
በሀገሪቱ ውስጥ ባሉ የውጭ ዜጎች ላይ የተነጣጠሩትን መጤ ጠል እንቅስቃሴዎችን ለመግታትና አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ፤ የሀገሪቱ መንግስት የሚያደረግው ጥረት አነስተኛ መሆኑም ተናግረዋል ኢትዮጵያውያኑ፡፡
“የደቡብ አፍሪካ መንግስት በተለያዩ አጋጣሚዎች ለይስሙላህ ከሚያወጣቸው መግለጫዎች በዘለለ ‘አልመረጥም’ የሚል ስጋት ስላለው ድርጊቱን ለማስቆም ይህ ነው የሚባል የወሰደው እርምጃ የለም”ም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያኑ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለውን በደል ለማስቆም እስካሁን ያደረገው ጥረት አነስተኛ ነው የሚል ቅሬታ እንዳላቸውም ለአል-ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
አስካሁን መጠኑ በውል ያልታወቀ የኢትዮጵያውያን ንበረትና ሃብት በህገ-ወጥ እንቅስቃሴው መዘረፉ ያነሱት ኢትዮጵያውያኑ፤ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኢትዮጵያውያንን ደህንነት ለማስጠበቅ ይህ ነው የሚባል ጥረት ሲያደረግ እንዳላዩም ተናገርዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዜጎችን ደህንነት ለማስጠበቅ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ለአል ዐይን አማርኛ ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ከሶስት ሚሊዮን የሚልቁ ዜጎቿ ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ በተለያዩ የዓለማችን ሀገራት እንደሚኖሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለስ አለም ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
አምባሳደር መለስ አለም ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት “አሁን ላይ በደቡብ አፍሪካ ከተሞች ያሉ ኢትዮጵያዊያን ከሌሎች ዜጎች በተለየ የደህንነት ችግር እንዳለባቸው አልሰማንም፤ ነገር ግን የዜጎቻችን ለማስጠበቅ እየሰራን ነው”ም ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ተነጋግረን ችግር ካለ ከደቡብ አፍሪካ መንግስት ጋር እንወያይበታለን ሲሉም አክለዋል ቃል አቀባዩ፡፡
በአሁኑ ወቅት የተባባሰው እና በደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ የውጭ ዜጎች ዘንድ የተፈጠረው ስጋት አዲስ አይደለም፤ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ጥቃቶች ሲያጋጥሙ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።
እንደፈረንጆቹ በ2008 በመላ ሀገሪቱ በስደተኞች ላይ በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ60 በላይ ሰዎች መገደላቸውና በሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ መፈናቀላቸው አይዘነጋም፡፡
እንደፈረንጆቹ በ2015ም እንዲሁ በደርባን እና በጆሃንስበርግ ከተሞች በውጭ ዜጎች ላይ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ መንግስት ወታደሮቹን ለማሰማራት የተገደደበት አጋጠሚ የሚረሳ አይደለም፡፡
ከአምስት ዓመት በፊት በተፈጸመ ሌላ ጥቃትም እንዲሁ በመቶዎች የሚቆጠሩ ናይጄሪያውያን ሀገሪቱን ለቅቀው ለመውጣት ተገደዋል።
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ እና ሌሎች የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በውጭ ዜጎች ላይ የሚፈጸሙ የጥላቻ ጥቃቶችን አጥብቀው በማውገዝ ስርዓት እንደሚያሰፍኑ በተደጋጋሚ ቢናገሩም፣ አደገኛው ጥቃት ጊዜ እየጠበቀ በማገርሸት የውጭ ዜጎችን ንብረትና ህይወት አደጋ ላይ እየጣለ ይገኛል።