ደቡብ አፍሪካ የደ ክለርክን ሞት ተከትሎ አራት ብሔራዊ የሃዘን ቀናትን አወጀች
ደ ክለርክ የአፓርታይድ ስርዓት እንዲያበቃ ያደረጉ የመጨረሻው ነጭ የደቡብ አፍሪካ መሪ ናቸው
የሃገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ እስከ ዕሁድ ዓላማ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል ተብሏል
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎዛ የቀድሞው የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ህልፈትን ተከትሎ የአራት ቀናት ብሔራዊ ሃዘን ማወጃቸው ተገለጸ፡፡
ሃሙስ ዕለት ሕልፈታቸው በተሰማው የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ቬሌም ደ ክለርክ የተነሳ በሀገሪቱ የአራት ቀናት ሃዘን መታወጁን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ጽፈዋል፡፡
በዚህም መሰረት በደቡብ አፍሪካ ከረቡዕ እስከ ዕሁድ የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ ይውለበለባል ተብሏል፡፡
የቬሌም ደ ክለርክ ቤተሰቦች የአስክሬን ማቃጠልና የቀብር ስነ ስርዓት በግላቸው ያዘጋጁ ሲሆን መንግስት ግን በቀጣይ ቀናት ብሔራዊ የመታሰቢያ ዝግጅት እንደሚያዘጋጅ ይጠበቃል፡፡
የጃኮብ ዙማን እስር ተከትሎ ደቡብ አፍሪካ በተፈጠረው ሁከት የሟቾች ቁጥር 337 ደርሰ
የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት፤ መንግስት የቀድሞውን የሀገሪቱን መሪ ቤተሰቦች እና ፋውንዴሽናቸውን ማነጋገሩን አስታውቋል፡፡ በቀጣይ ዕሁድ በሚኖር የመታሰቢያ ዝግጅት ላይ የመንግስታት መሪዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎች እና የሲቪል ማህበራት ተወካዮች እንደሚገኙ ነው የተገለጸው፡፡
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ቬሌም ደ ክለርክ ቀብር ስነ ስርዓት ዕሁድ እንደሚፈጸም ፋውንዴሽናቸው ይፋ አድርጓል፡፡
የአፓርታይድ አገዛዝ እንዲያበቃ እና እና ከነጻነት በኋላ የመጀመሪያ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ነጻ ሆነው ሀገሪቱን እንዲመሩ ሁኔታዎችን ያመቻቹት ደክለርክ ናቸው፡፡
ደ ክለርክ የመጨረሻው የደቡብ አፍሪካ ነጭ ፕሬዝዳንት ሲሆኑ የህልፈታቸው መንስዔም የካንሰር ህመም መሆኑ ተገልጿል፡፡ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በ85 ዓመታቸው ነው፡፡