አንድ ሰው በሶስት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ የቦርድ አመራር እንዲሆን የሚፈቅደው ህግ ጥያቄ ተነሳበት
በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲግ ግሩፕ የተሰጠው የተጋነነ ስልጣን እንዲቀንስ ለመንግሥት ጥያቄ ቀረበለት
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ውጪ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ብድር መበደር እንደማይችሉ መንግሥት አስታወቀ
አንድ ሰው በሶስት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ውስጥ የቦርድ አመራር እንዲሆን የሚፈቅደው ህግ ጥያቄ ተነሳበት።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በመንግስት የልማት ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።
የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ከምክር ቤቱ አባላት በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ላነሷቸው ጥያቄዎች በምክር ቤቱ ተገኝተው ምላሽ ሰጥተዋል።
የምክር ቤቱ አባላት ከ60 በላይ ጥያቄዎችን በረቂቅ አዋጁ ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጧቸው ለሚንስትሩ አቅርበዋል።
ከተነሱ ጥያቄዎች መካከልም ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲግ ግሩፕ የተጋነነ ስልጣን ተሰጥቷል፣ የልማት ድርጅቶችን የማፍረስ እና የማዋሀድ ስልጣን መሰጠቱ፣ የቦርድ አባላት አሿሿም፣ ትርፍ ክፍፍል፣ ተቋማትን ወደ ግል ማዞር፣ ብድር መውሰድ እና ሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በራሱ እንዲወስን የሚያደረጉ ስልጣን እና ሀላፊነት መሰጠቱ ትክክል አለመሆኑን የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።
ማንኛውም የቦርድ አባል ከሶስት ለማይበልጡ ተወዳዳሪ ላልሆኑ የመንግስት የልማት ድርጅቶች በተመሳሳይ ጊዜ በቦርድ አባልነት በመሾም ሊያገለግል ይችላል በሚል በረቂቅ አዋጁ ላይ መካተቱ ከተቋማት ውጤታማነት አንጻር ትክክል እንዳልሆነም ተነስቷል።
ሌላኛው በምክር ቤት አባላት የተነሳው ጥያቄ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ለስራ ማከናወኛቸው ከ6 እስከ 18 ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ የሚከፈል ብድር መዋዋል እንደሚችሉ ቢገልጽም ተቋማቱ መበደር የሚችሉት የገንዘብ መጠን ሊወሰን ሲገባ ይህ ለምን አልተደረገም የሚለው ጉዳይ ነው።
የልማት ድርጅቶች አመራር ምደባ ብቃትን መሰረት ባደረገ መንገድ መሆን ያለበት ቢሆንም የብሄር፣ ጾታ፣ አካል ጉዳተኝነትን እና ሌሎች የሀገሪቱ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ ባስገባ መንገድ እንዲሆን የሚፈቅድ አሰራር ሊካተት ይገባል የሚለው ጥያቄም ከምክር ቤቱ አባላት ተነስቷል።
የገንዘብ ሚንስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው ኢትዮጵያ ላለባት የብድር ጫና ምክንያት የልማት ድርጅቶች ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ አበዳሪዎች የተበደሩት ገንዘብ መጠን አንዱ መሆኑን ተናግረዋል ።
የነዚህን ተቋማት ትርፍ ለማሳደግ ሲባልም ያለባቸውን ብድር መንግሥት በመውሰድ የተሻለ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው ሲባል መንግሥት ብዙ ድጋፎች ማድረጉንም ሚንስትሩ ገልጸዋል።
የብድር ጫናውን ለመቀነስ ሲባልም ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የወለድ ምጣኔያቸው ከፍተኛ የሆኑ የንግድ ብድር ከየትኛውም አካል አለመበደሯን በምላሻቸው ጠቅሰዋል።
የብድር ጫናውን ለመቀነስ እና የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ውጤታማ ለማድረግ ሲባል የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲግ ግሩፕ እንደተቋቋመ የተናገሩት አቶ አህመድ ይህ ተቋማ ውጤታማ እንዲሆን የግድ የውሳኔ አሰጣጥ ነጻነት እንዲኖረው መደረጉንም አንስተዋል።
ነገር ግን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ግሩፕ የስራ እና የውሳኔ ነጻነት ተሰጠው ማለት ሀላፊነት በተሞላበት እና ግልጽ የቁጥጥር ስርዓትን አይከተልም ማለት አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።
የመንግስት የልማት ድርጅት ወደ ግል እንዲዞር ሲፈለግ፣ ተቋማት እንዲፈርሱ ሲደርግ እንዲሁም አዲስ የልማት ድርጅት ሲቋቋም የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲግ ግሩፕ ቦርድ ከውጤታማነት አንጻር ውሳኔ እንዲያሳልፍ ቢደረግም የመጨረሻ ውሳኔ የሚያሳልፈው ግን የሚንስትሮች ምክር ቤት እንደሆነ አቶ አህመድ ለምክር ቤቱ አባላት በሰጡት ምላሽ ላይ ተናግረዋል።
ሁሉም የመንግስት የልማት ድርጅቶች በራሳቸው ለስራ ማከናወኛቸው ብድር እንዲበደሩ የሚፈቅድላቸው ህግ ያለ ቢሆንም ብድሮቹ ተጠራቅመው ሀገር ላይ ጫና እየፈጠሩ በመሆኑ ምክንያት አሰራሩ የተጠና እና የተማከለ እንዲሆን መደረጉም ተገልጿል።
አሁን ላይ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ በስተቀር ሌሎች የመንግስት የልማት ድርጅቶች የንግድ ብድሮችን መውሰድ አይችሉም ተብሏል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወዳዳሪነቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በመሆኑ እና ጥራት ያለው፣ ግልጽ የፋይናንስ ሪፖርት ስላለው ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አበዳሪዎች መበደር እንደሚችል ተገልጿል።
መንግስትም የአየር መንገዱን ውጤታማነት ለመጨመር ከእዳ ነጻ እንዳደረገው የተናገሩት ሚንስትሩ እንደ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ ግዙፍ የልማት ድርጅቶችም የኢትዮጵያ አየር መንገድን መንገድ እንዲከተሉ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑም ተጠቅሷል።
በምክር ቤቱ አባላት የተነሱ ጥያቄዎችን እና የተሰጡ አስተያየቶችን መነሻ በማድረግ ፣እንዲሁም በቀጣይ በሚደረጉ ተጨማሪ ውይይቶች ላይ የሚነሱ ግብረ መልሶች በረቂቅ አዋጁ ላይ ማሻሻያዎች እና ማስተካከያዎች እንደሚደረጉ ተገልጿል።