የፓስፖርት ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር በአንጻራዊነት መቀነሱ ተገለጸ
አሁን ላይ ፓስፖርት የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር ከ300 ሺህ ወደ 190 ሺህ ዝቅ ብሏል ተብሏል
ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ ለ110 ሺህ ኢትዮጵያዊያን ፓስፖርት መሰጠቱ ተገልጿል
የፓስፖርት ፈላጊ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር በአንጻራዊነት መቀነሱ ተገለጸ።
በአገልግሎት አሰጣጡ ምክንያት ሁሉንም ከፍተኛ አመራሮች ከሀላፊነት በማንሳት አዲስ አመራር የተሾመለት የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት የተለያዩ ማሻሻያዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑን አስታውቋል፡፡
ባሳለፍነው ሀምሌ ወር ላይ ተቋሙን በሀላፊነት እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር) የተሾሙት ወ/ሮ ሰላማዊት ዳዊት በፓስፖርት አሰጣጥ እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ሀላፊው በዚህ ጊዜ እንዳሉት በኢትዮጵያ የፓስፖርት ፈላጊዎች ቁጥር 300 ሺህ እንደነበር ገልጸው 110 ሺህ ዜጎች ፓስፖርት አግኝተዋል ብለዋል።
አሁን ላይ ፓስፖርት እንዲያገኙ ለኢምግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት ያመለከቱት ዜጎች ቁጥር 190 ሺህ እንደሆኑም ተገልጿል።
ተቋሙ ባለፉት ሶስት ወራት በሰራቸው ስራዎች ከ531 ሺህ በላይ ፓስፖርት ታትሞ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል ያሉት ሀላፊዋ 43 ሺህ 366 ለሚሆኑ በአዲስ አበባ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ፓስፖርት ተሰጥቷልም ብለዋል።
እንዲሁም 15 ሺህ 793 ለሆኑ ዜጎች ደግሞ ለአስቸኳይ ፓስፖርት ፈላጊዎች ሲሰጥ 8 ሺህ 500 ለሚሆኑ በክልሎች ለሚኖሩ ዜጎችም ፓስፖርት እንደተሰጡ ተገልጿል።
ይሁንና ፓስፖርት እንዲሰጣቸው ካመለከቱ ሰዎች ውስጥ 15 ሺህ 924 ሰዎች ፓስፖርታቸውን መጥተው እንዲወስዱ የጽሁፍ መልዕክት ቢላክላቸውም አልወሰዱም ተብሏል።
ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት አክለውም ከፓስፖርት አሰጣጥ ጋር በተያያዝ የስነ ምግባር ጥሰት ፈጽመዋል የተባሉ 38 የተቋሙ ሰራተኞችም በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጋቸውንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የመዳረሻ ቪዛን ወይም ቪዛ ኦን አራይቫል አገልግሎትን ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ጀምሮም በመስጠት ላይ መሆኗን ወይዘሮ ሰላማዊት በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።
"የመዳረሻ ቪዛ ከ120 ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ለሚገቡ ጎብኚዎች በመስጠት ላይ እንገኛለን" ሲሉ የተናገሩት ሀላፊው በአገልግሎቱ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎችን ቀስ በቀስ እየፈተን እንሄዳለንም ብለዋል።