በረቂቅ አዋጁ ላይ ቀደም ሲል የተወያየው ምክር ቤቱ በአብላጫ የድጋፍ ድምጽ ነው ረቂቅ አዋጁን ያጸደቀው
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበለትን ረቂቅ አዋጅ አጸደቀ፡፡
ምክር ቤቱ ዛሬ ባካሄደው 2ኛ ልዩ ስብሰባው ከሕግ፣ ፍሕት እና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ ነው ረቂቅ አዋጁን ያጸደቀው።
አዋጁም በ13 ተቃውሞና በአንድ ድምጸ ተዓቅቦ አዋጅ 1265/2014 ሆኖ ነው በአብላጫ ድምፅ ጸድቋል።
ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ተደርጎበት በተገኙ ግብዓቶች መሰረት በአንቀጾች ላይ ክለሳና ማስተካከያ ተደርጎ መጽደቁ የተነገረለት ረቂቅ አዋጁ በተለያዩ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባትን ለመፍጠር በማሰብ ተዘጋጅቷል ተብሏል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ላይ ከሰሞኑ ይፋዊ የህዝብ ውይይት እንደተካሄደበት ምክር ቤቱ በይፋዊ ማህበራዊ ገጹ አስታውቋል፡፡
በውይይቱ ማቋቋሚያ አዋጁንና ኮሚሽኑን የተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የፍትህ ሚኒስትሩ ጌዲዮዎን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) ስለ ኮሚሽነሮች ሹመት እና ኮሚሽነሮቹ መሉ ጊዜያቸውን ስራ ላይ የሚያውሉ እንደሆነ አስረድተዋል።
ሆኖም የውይይቱ ተሳታፊዎች ኮሚሽኑ እውነተኛና ችግር ፈቺ ሆኖ እንዲቋቋም መጠየቃቸውን ያስታወቀው ምክር ቤቱ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት ይሾማሉ ስለተባሉ ኮሚሽነሮች ገለልተኛነትና ከገንዘብ ሚኒስቴር የሚገኝ ነው ስለተባለው የኮሚሽኑ የበጀት ጉዳይ ጥያቄዎች ጠይቀዋል፡፡
ኮሚሽነሮቹ ከፖለቲካ፣ ከሃይማኖት እና ከብሄር ወገንተኝነት የፀዱ፣ ችሎታና ብቃታቸው የተረጋገጠ፣ እንዲሁም አገርና ህዝብን ለማሻገር ቁርጠኛ የሆኑ ህዝብ ያመነባቸው ሊሆኑ እንደሚገባም ነው በውይይቱ የተነሳው።
የረቂቅ አዋጁ ርዕስ አገራዊ የምክክር መድረክ ከማለት ይልቅ ‹‹ብሄራዊ የመግበባት መድረክ›› ቢባል የሚሻል እንደሆነም አንስተው ነበር፡፡
ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት ጌዲዮዎን ጢሞቲዮስ (ዶ/ር) በበኩላቸው አገራዊ የምክክር መድረኩ ዋና አላማ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እስከሆነ ድረስ በርዕሱ ላይ ማሻሻያ ሊደረግበት እንደሚችል ተናግረዋል።
የልዩነቶች ምንጭ በሆኑ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር እንዲደረግና ብሔራዊ መግባባት እንዲመጣ በተለያዩ አካላት ሲጠየቅ ነበረ፡፡
መንግስትም በጥያቄዎቹ መሰረት ሃገራዊ ምክክሮችን ለማድረግ ቃል ገብቶ ነበር፡፡ ኮሚሽኑ በዚሁ መሰረት ስለመቋቋሙም ነው የተነገረው፡፡
ከሰሞኑ ከአናዶሉ ጋር በነበራቸው ቆይታ ጉዳዩን የተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ሁሉን ያካትታል ባሉት ውይይት ህገ መንግስቱን ማሻሻልን ጨምሮ በርካታ ሃገራዊ ጉዳዮች ለውይይት ክፍት እንደሚሆኑ መናገራቸው ይታወሳል፡፡