ጎንደር ዩኒቨርስቲ ‘‘ህወሓት በጅምላ ለጨፈጨፈው’’ የወልቃይት፣ ጠገዴ እና ጠለምት ህዝብ ሙዚየም እንዲያቋቁም ምክረ ሃሳብ ቀረበ
ሚዛናዊ አይደለም በሚል የእነ አምነስቲን ሪፖርት ውድቅ ያደረገው የአማራ ክልል መንግሥት ሪፖርቱን እንደማይቀበል አስታውቋል
ዩኒቨርስቲው የዘር ማጥፋት ማዕከል እንዲያቋቁምና ትውልድ እንዲማርበትም ተጠይቋል
ጎንደር ዩኒቨርስቲ ‘‘በህወሓት በጅምላ ተጨፍጭፏል’’ ለተባለለት የወልቃይት፣ የጠገዴ እና ጠለምት ህዝብ መታሰቢያ ሙዚየም እንዲያቋቁም ተጠየቀ፡፡
ጥያቄው ዩኒቨርስቲው ባቋቋመውና ለባለፉት አንድ ዓመት ከሶስት ወራት ህወሓት በወልቃይት፣ ጠገዴና ጠለምት ህዝብ ላይ ዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸም አለመፈጸሙን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ባጠናው የምሁራን ስብስብ የቀረበ ነው፡፡
ከተለያዩ የሙያ መስኮች የተውጣጡ 21 ምሁራንን ማካተቱን ያስታወቀው የጥናት ቡድኑ የጥናቱን ቅድመ ግኝት ይፋ ባደረገበት ባሳለፍነው ሐሙስ መጋቢት 29 ቀን 2014 ዓ/ም በጎንደር ከተማ በሰጠው መግለጫ ህወሓት በወልቃይት ጠገዴና ጠለምት ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈፀሙን በጥናት ማረጋገጡን አስታውቋል።
ጥናቱ ህወሓት ወደ ወልቃይትና አካባቢው ተሻግሮ ጥቃቶችን መፈጸም ከጀመረበት ከ1972 ዓ/ም ጀምሮ አካባቢውን ለቆ እስከወጣበት እስከ 2013 ዓ/ም ድረስ ያሉትን አመታት የሚሸፍን ነው ያሉት የቡድኑ መሪ ጌታ አስራደ (ረ/ፕ/ር) የአካባቢውን ማህበረሰብ በማንነት ለይቶ ሲያፈናቅል፣ ሲያፍንና ሲገድል እንደነበር በጥናቱ አረጋግጠናል ብለዋል።
ህጋዊ የሰፈራ መርሃ ግብሮች ባልነበሩበት ወቅት በሰፈራ ስም ወረራ በማካሄድ ነባሩን የአካባቢውን ነዋሪ ያፈናቅል እንደነበር መረጋገጡን ገልጸዋል፤ ከርስቱ የተፈናቀለው ነባሩ ህዝብ አጎራባች የክልሉን አካባቢዎች ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱና የዓለም ክፍሎች ተበታትኖ በስደት ለመኖር መገደዱን በመጠቆም፡፡
ንድፈ ሃሳቡ በወጉ ተገምግሞ የተካሄደ ነው በተባለውና 6 ወረዳዎችንና 6 ከተሞችን ባካለለው ጥናት 912 አባዎራዎች እና 75 ተቋማት ተጠይቀዋል።
በጥናቱ መሰረትም ህወሓት በስልታዊ እና መዋቅራዊ መንገዶች ወንጀሎችን ሲፈጽም እንደነበር የጥናቱ ግኝቶች አመልክተዋል።
ግኝቶቹ ህወሓት በዓለም አቀፍ ወንጀል የሚያስጠይቁ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን መፈጸሙን ማመልከታቸውንም ነው የቡድኑ መሪ የተናገሩት። ይህን የሚያሳዩ ጅምላ መቃብሮች መገኘታቸውንም ገልጸዋል። የቅርቡን የማይካድራውን ይጨምራሉ የተባለላቸው ጅምላ መቃብሮቹ መግለጫው እስከተሰጠበት ቀን ድረስ ከ12 በሚበልጡ የተለያዩ ቦታዎች የተገኙ ናቸው።
ህወሓት አደራጅቶታል በተባለው እና “ሳምሪ” በተሰኘው ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በማይካድራና በአካባቢው በተፈጸመው ጭፍጨፋ ከ600 የሚልቁ ንጹሃን ተገድለዋል ያለው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጭፍጨፋው በጦር ወንጀለኝነት ጭምር ሊያስጠይቅ የሚችል “የግፍና የጭካኔ ወንጀል” ነው ሲል ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
ጭፍጨፋው በርካታ ንፁሃን የተገደሉበት ዓለም አቀፍ የሽብር ወንጀል ሆኖ በዓለም አቀፉ የፖሊስ ተቋም (ኢንተርፖል) መመዝገቡም የሚታወስ ነው፡፡
የማይካድራውን ጭፍጨፋ ጨምሮ ‘ገሃነም’ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ ድብቅ ጅምላ መቃብሮች ሳር በቅሎባቸው መገኘታቸውም ተገልጿል፡፡ ቃሌማ በሚል ስያሜ በተለያየ ኮድ የተሰየሙ ጅምላ መቃብሮችን ማግኘቱንም ነው የጥናት ቡድኑ ያስታወቀው።
ሆኖም ጉዳዩ ከፍ ያለ የወንጀል፣ የሞራልና የሰብዓዊነት ጉዳይ መሆኑን ተከትሎ ቅድመ ጥናቱ ይፋ ቢሆንም ጥናቱ ገና ሙሉ በሙሉ አልተጠናቀቀም፡፡ ከተወሰኑ መቃብሮች ናሙና በመውሰድ ጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ለማየት ቢቻልም በፎረንሲክና ሌሎች ሳይንሳዊ ምርመራዎች ማረጋገጥ ይቀሩታልም ተብሏል።
ለዚህም የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ የፌዴራል የፍትህና ሌሎች ተቋማት ምርመራውን እንዲያግዙ እና ተጠያቂነትም እንዲሰፍንም ነው ቡድኑ ጥሪ ያቀረበው፡፡
በስተመጨረሻም የጥናት ቡድኑ ዩኒቨርስቲው የዘር ማጥፋት ማዕከል እንዲያቋቁም ጠይቋል፡፡ ትውልድ ሊያስተምር በሚችል መልኩ የጅምላ ጭፍጨፋው ሰለባዎች አጽም ተሰብስቦ በአንድ ማዕከል በሙዚየም እንዲቀመጥም ምክረ ሃሳብ አቅርቧል፡፡
የጥናት ቡድኑን ገልለተኛነትና የግኝቱን ተዓማኒነት ለማስጠበቅ ከጥናት ንድፈ ሃሳቡ ጀምሮ ኃላፊነት በተሞላበትና ሙያዊ ስነ ምግባርን በጠበቀ መልኩ እየተገመገመ ሲሰራ እንደነበርና የተገኘው እያንዳንዱ የሰነድ፣ የድምጽና የምስል መረጃና ማስረጃ ሙያዊ በሆነ ሳይንሳዊ መንገድ ተሰንዶ መቀመጡንም አጥኚዎቹ ገልጸዋል፡፡
አምነስቲ እና ሂውማን ራይትስ ዎች ከሰሞኑ በምዕራብ ትግራይ በዋናነት በትግራይ ተወላጆች ላይ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች መፈጸማቸውን የሚያትት የምርመራ ሪፖርት በማውጣት የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ኃይል በአካባቢው እንዲሰማራ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
ጥያቄውንና ሪፖርቱን በተመለከተ የተጠየቁት የአጥኚ ቡድኑ አባላት እርስበርሱ የሚጣረስና የሚጋጭ ከፍተኛ ችግር እንዳለበት በመጠቆም ከእውነታ ይልቅ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው ብለዋል፡፡
ሪፖርቱ በመግቢያው የወልቃይት፣ የጠገዴ እና ጠለምት አካባቢ በደርግ ጊዜ በተጠናና ታሪክን መሰረት ባደረገ መልኩ ወደ ትግራይ እንደተካለለ አድርጎ ማስቀመጡ ምን ያህል ታሪክና እውነታዎች ተዛብተው እንደቀረቡበት መሳያ መሆኑንም ነው የጠቀሱት፡፡
ለሪፖርቱ ግብዓት የሆኑ አብዛኛዎቹ መረጃዎች ዘፈቀዳዊ በሆነ መልኩ በስልክ እንዲሁም በሳታላይት የተሰበሰቡ ናቸው መባሉ ተዓማኒነቱን እንደሚያጎድልም አብራርተዋል አጥኚዎቹ፡፡
ጥናታቸው የተሟላና ከእነ አምነስቲ ጋር የሚወዳደር እንዳልሆነ በማስታወቅም ለሚፈልግ የትኛውም አካል መረጃዎቹን በመስጠት ለመተባበር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ገለልተኛነት፤ ሚዛናዊነት እና ተዓማኒነት ይጎድለዋል በሚል የእነ አምነስቲን ሪፖርት ውድቅ ያደረገው የአማራ ክልል መንግሥት ሪፖርቱን እንደማይቀበል ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
እነ አምነስቲ በሀገር ውስጥ የወሰን ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደማይችሉ በማሳሰብ መግለጫ ያወጣው መንግስት፤ የሪፖርቱን ይዘት በጥንቃቄ እንደሚመረምር ማስታወቁም አይዘነጋም፡፡