ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ከአቶ አሻድሊ ሀሰንና ከምክትላቸው ጋር በግልገል በለስ በዝግ እየተወያዩ ነው
ጠዋት ላይ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አመራሮች ከዞኑ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል
በመተከል ዞን ግልገል በለስ ከተማ ያሉ መስሪያ ቤቶች በሙሉ ተዘግተው እንደሚገኙ አል ዐይን አረጋግጧል
የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕብረት መረጃ ዋና መምሪያ ሀላፊ ሌ/ጄ አስራት ዴኔሮ ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰንና ከምክትላቸው ጌታሁን አብዲሳ ጋር በዝግ እየተወያዩ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
በግልገል በለስ ከተማ ውስጥ ስታር ሆቴል እየተካሄደ ባለው ዝግ ስብሰባ የዞን አመራሮች እንዲወጡ መደረጉን ለማወቅ ችለናል፡፡ የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አትንኩት ሽቱን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች ውጭ እንዲሆኑ መደረጉን አል ዐይን ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
አል ዐይን ኒውስ ከዞኑ ዋና አስተዳዳሪ በስልክ እንዳረጋገጠው ጠዋት ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ከዞኑ አመራሮች ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡ አቶ አትንኩት እንዳሉት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ሕብረት መረጃ ዋና መምሪያ ሀላፊ ሌ/ጄ አስራት ዴኔሮን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የጦር መሪዎች በመተከል እየተወያዩ ነው፡፡ በመተከል ከሚፈጸመው የንጹኃን ጭፍጨፋ ጋር በተያያዘ የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊን ጨምሮ በሕግ ቁጥጥር ስር የዋሉ አመራሮች መኖራቸውን ተከትሎ ፣ ሌሎች አመራሮችስ እጃቸው የለበትም ወይ የሚል ጥያቄ የተነሳላቸው አቶ አትንኩት የተጠረጠሩት አመራሮች ተይዘዋል እኛ ስራ እየሰራን ነው ብለዋል፡፡
አሁን ላይ የመከላከያ ከፍተኛ አመራሮች ከአቶ አሻድሊ እና አቶ ጌታሁን ጋር እየተወያዩ መሆኑንም አቶ አትንኩት አረጋግጠዋል፡፡
በግልገል በለስ ከተማ ያሉ መስሪያ ቤቶች በሙሉ መዘጋታቸው የተገለጸ ሲሆን ከተማዋ ጸጥ ያለ ድባብ ውስጥ መሆኗም ተጠቅሷል፡፡
በግልገል በለስ ስታር ሆቴል ውስጥ የሚደረገውን ውይይት ተከትሎ የተለያየ እርምጃ የሚወሰድባቸው የከፍተኛ አመራሮች እንደሚኖሩ ይጠበቃልም ብለዋል፡፡