ኢሰመኮ ባደረገው ማጣራት በቡለን ወረዳ የበኩጂ ቀበሌ ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ገለጸ
በሰው ሕይወት እና በአካል ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ የደረሱ ሰብሎችና የተሰበሰቡ ማሳዎች በእሳት ጋይተዋል
በስምና በመልክ የሚያውቋቸው "የበኩጂ ቀበሌ ነዋሪዎች ጭምር በጥቃቱ መሳተፋቸውን" የተረፉ ተጎጂዎች ገልጸዋል
ታኅሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ከለሊቱ 10፡00 ሰዓት ላይ የታጠቁ ኃይሎች በእንቅልፍ ላይ በነበሩ ነዋሪዎች ላይ በለኮሱት እሳት እና በተኩስ ከ100 በላይ ሰዎች መገደላቸው በክልሉ ያለው የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ በከፍተኛ ሁኔታ እየተዳከመ መሄዱን እንደሚያሳይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ገለጸ።
ኢሰመኮ የጥቃቱን ሂደት በተመለከተ ታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ከሚመለከታቸው አካላት እና ከተጎጂዎች ጋር በመነጋገር ሲከታተልና ሲያጣራ መቆየቱን ምሽት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። በኩጂ ቀበሌ ከወረዳው መቀመጫ ከሆነችው ቡለን ከተማ 90 ኪ.ሜ. ርቃ የምትገኝ ሲሆን የሺናሻ፣ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች ይኖሩባታል። ለቀበሌው የተመደበ የፖሊስ ወይም የፀጥታ ኃይል አለመኖሩን ኮሚሽኑ በክትትሉ መረዳቱን ነው የገለፀው።
ኮሚሽኑ ሁኔታውን እስካጣራበት ጊዜ ድረስ በቡለን ሆስፒታል 36 ተጎጂዎች እርዳታእየተደረገላቸው ሲሆን አብዛኞዎቹ በጥይት፣ ሌሎቹ በቀስት የቆሰሉ መሆናቸውን በምልከታ አረጋግጧል። በተጨማሪም ሰዎች ጥቃት የደረሰባቸውን ሁኔታ የሚያሳዩና የሚረብሹ የፎቶግራፍ ማስረጃዎች ለኮሚሽኑ ደርሰውታል። በሰው ሕይወት እና በአካል ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ የደረሱ ሰብሎችና የተሰበሰቡ ማሳዎች በእሳት ጋይተዋል። ቢያንስ 18 ያክል ነዶዎች ሲቃጠሉ ማየታቸውን አንድ ተጎጂ አስረድተዋል።
በጨላንቆ እና ዶሼ ቀበሌዎች ቤቶች እየተቃጠሉ እንደሆነ ከአካባቢው ለኮሚሽኑ የተላኩ መረጃዎች ያመለክታሉ። በድባጤ ወረዳ ዶንበን ቀበሌ ስጋት የገባቸው ነዋሪዎች ከታኅሣሥ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ ቀዬአቸውን ጥለው እየተሰደዱ እንደሆነም ኮሚሽኑ ተረድቻለሁ ብሏል።
አካባቢውን በቅርበት እንዲጠብቅ የተመደበው ብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት ታኅሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ.ም. ለማረጋጋት ተግባር ወደቦታው ተልከው የነበሩ አንድ የፌዴራል እና ሁለት የክልሉ አመራሮችን ለማጀብ በሚል አካባቢውን ለቅቆ መሄዱ ታውቋል። ጥቃቱ የጀመረው ይህንኑ ተከትሎ እንደሆነና ሌሊቱን የጀመረው ጥቃት እስከ ቀኑ አጋማሽ ድረስ መዝለቁንም ለማወቅ ተችሏል። ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው ተጎጂዎች እንደሚሉት በጥቃቱ ከሞቱ ሰዎች መካከል አብዛኛው የሺናሻ ተወላጆች ናቸው።
ከዚህ ቀደም በነበሩ ጥቃቶች ፈጻሚዎቹ ከ”ጫካ” የሚመጡ ሰዎች የነበሩ ቢሆንም፣ በዚህኛው ጥቃት “በስምና በመልክ የሚያውቋቸው "የበኩጂ ቀበሌ ነዋሪዎች ጭምር መሳተፋቸውን" ከጥቃቱ የተረፉ ተጎጂዎች ገልጸዋል።
ኢሰመኮ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የሚከሰቱ ጥቃቶችን ተደጋጋሚነትና የክልሉን ሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ሁኔታ አስመልክቶ፣ የፌዴራሉንና የክልሉን መንግሥታት የተጠናከረ ትብብርና ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሻ ሲያሳስብ መቆየቱ ይታወሳል። ይሁንናጥቃቶቹ በመልክ እና በስፋት እየተባባሱ መጥተዋል።
ስለሆነም፣ በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸው እና ለተፈናቀሉ ሰዎች የህክምና እና ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀርብ፣ እንዲሁም ተገቢው ማጣራትና ጥቃቱን ባለመከላከልም ሆነ በሌላ መልኩ ጥቃቱን የፈጸሙና ያባባሱ ሰዎችን ሕግ ፊት የማቅረቡ ሂደት ከወዲሁ እንዲጀመር ኮሚሽኑ አሳስቧል። በአካባቢው የሚገኘው የፀጥታ ኃይልና መዋቅር የሰዎችን ደኅንነት ሙሉ በሙሉ ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ በከፍተኛ ደረጃ በአፋጣኝ እንዲጠናከርም ኢሰመኮ ጥሪ አቅርቧል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት የተባሉ አመራሮችን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደጀመረ እና በዛሬው እለትም 5 አመራሮችን መያዙን አስታውቋል።
በዚህም መሠረት፡-
1ኛ. አቶ ቶማስ ኩዊ፡- የኢፌዴሪ ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ
2ኛ. አቶ አድጎ አምሳያ፡- የቀድሞው የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር
3ኛ. አቶ ሽፈራው ጨሊቦ፡-የቀድሞ የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር
4ኛ. አቶ ባንዲንግ ማራ፡- የመተከል ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ
5ኛ. አረጋ ባልቢድ፡- የመተከል ዞን የቀድሞ አመራር የነበሩ በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል።