ከኮሮና ጋር በተያያዘ በሀገሪቱ የጤና ባለሙያዎች ላይ የሚፈጸም ጥቃት እየተባባሰ ነው ተብሏል
ሱዳን የጤና ባለሙያዎችን የሚጠብቅ ፖሊስ ልታሰማራ ነው
የኮሮቫ ቫይረስ ወረርሽኝ በተስፋፋበት ጊዜ በጤና ሰራተኞች እና በሆስፒታሎች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶች እየጨመሩ በመሄዳቸው የሱዳን የሽግግር ባለስልጣናት የጤና ሰራተኞችን እና ተቋማትን ለመከላከል የፖሊስ ኃይል ለመመደብ እየሰሩ መሆናቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ገለፀ፡፡
መንግስት ይህን እርምጃ ለመውሰድ የወሰነው ፣ ባለሥልጣናት ለጤና ሰራተኞች እና ለጤና ተቋማት ጥበቃ እንዲሰጡ ግፊት ለማድረግ በሚል ፣ በሀገሪቱ የሚገኙ ሐኪሞች የስራ ማቆም አድማ እንደሚያደርጉ ባለፈው ሐሙስ በመግለጻቸው ነው፡፡
ጠ / ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ በጤና ሰራተኞች ላይ የሚፈጸሙ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚወሰዱ ወሳኝ እና ጥብቅ መፍትሄዎችን በተመለከተ ከዶክተሮች ተወካዮች ጋር መነጋገራቸውን ጽህፈት ቤታቸው ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
መንግስት ለጤና ሰራተኞች ጥበቃ ለማድረግ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ያወጣልም ብሏል መግለጫው ፡፡
ባለፉት ሁለት ወራቶች በመላ ሀገሪቱ በጤና ሠራተኞች እና ተቋማት ላይ በርካታ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የሱዳን ሐኪሞች ኮሚቴ ይፋ አድርጓል፡፡
ባለፈው ወር በአንድ አጋጣሚ፣ በሀገሪቱ ኦምዱርማን ከተማ የሚገኝ አንድ ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ ህመምተኞችን ይቀበላል የሚል ወሬ ተሰራጭቶ በሆስፒታሉ ሁከት ተፈጥሮ ነበር፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ፖሊስ ህንፃውን ለማጥቃት የሞከሩ በርካታ ሰዎችን በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡
ባለፈው ሐሙስ ብቻ በካርቱም በጤና ሰራተኞች እና መገልገያዎች ላይ ቢያንስ ሦስት ጥቃቶች መከሰታቸውም ነው የተገለጸው፡፡
ሱዳን እስካሁን በኮሮኔቫቫይረስ በሽታ ከተያዙ 3,628 ያህል ሰዎች መካከል 146 የሚሆኑ ሰዎች መሞታቸውን ሪፖርት አድርጋለች፡፡
የሱዳን የጤና ስርዓት ለአስርት ዓመታት በነበረው ጦርነት እና ማዕቀቦች እንደተዳከመ ይነገራል። ሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አል-በሽርን ከስልጣን እንዲወርዱ ካደረገው ያለፈው ዓመት ህዝባዊ አመጽ ገና በማገገም ላይ ነች፡፡