በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል ኢትዮጵያና ሱዳን ያቀረቡትን ሀሳብ ግብጽ ተቀበለች
በህዳሴው ግድብ ዙሪያ የተጀመረው ድርድር እንዲቀጥል ኢትዮጵያና ሱዳን ያቀረቡትን ሀሳብ ግብጽ ተቀበለች
በታላቁ ህዳሴ ግድብ የዉሃ ሙሌት እና አለቃቅ ላይ ከኢትዮጵያ እና ሱዳን ጋር የተጀመረውን ድርድር ለመቀጠል ዝግጁ መሆኗን ግብጽ በዛሬው እለት አስታውቃለች፡፡
“ግብጽ ወደ ድርድር ለመመለስ እና በሶስቱ ሀገራት የዉሃና መስኖ ሚኒስትሮች ስብሰባ ለመሳተፍ ዝግጁ ነች” ሲል የሀገሪቱ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ “ጠንካራ እና ገንቢ ዉይይቶች ፍትሀዊ ፣ ሚዛናዊ እና አጠቃላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ ይረዳሉ” ሲልም ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡ የሚደረሰው ስምምነት የሶስቱንም ሀገራት የዉሃ ፍላጎት ከግምት ያስገባ ሊሆን እንደሚገባም መግለጫው ያትታል፡፡
የግብጽ ዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይህን መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያና የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትሮች በቪዲዮ ኮንፈረንስ ውይይት አድርገው በውኃ ሚኒስትሮቻቸው አማካኝነት የቴክኒክ ውይይቶችን ለመቀጠል እና ያልተቋጩ ጉዳዮችን ለማጠናቀቅ መስማማታቸውን ተከትሎ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትረ ዐቢይ አህመድ እና የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክ የህዳሴውን ግድብ የተመለከተውን የቴክኒክ ድርድር ለመቀጠል መስማማታቸውን ከውይይታቸው በኋላ አስታውቀዋል፡፡
ሀሙዶክ በሱዳን ካቢኔ ስብሰባ ባደረጉት ንግግር በሁለቱ ወገኖች በተካሄደው ውይይት ፣ በህዳሴው ግድብ የቅርብ ጊዜ ዕድገቶች ዙሪያ በኢትዮጵያ መንግስት ገለጻ እንደተደረገላቸው እንዲሁም በሱዳኑ ለተነሱት አሳሳቢ ጉዳዮች መልስ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡ ካርቱም ላነሳቻቸው ስጋቶች ፣ የአካባቢ ጉዳዮች ፣ የግድቡ ደህንነት እና የመረጃ ልውውጥ ማመቻቸት ዙሪያ ማብራሪያ እንደተሰጣቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ ገልጸዋል፡፡
በሶስቱ ሀገራት መካከል ከዚህ ቀደም ሲካሄድ የነበረው ድርድር ተጨማሪ ዝግጅት ያስፈልገኛል በሚል ኢትዮጵያ ባለፈው የካቲት ወር በዋሺንግተን ዲ.ሲ በተዘጋጀው የመጨረሻ ድርድር ባለመሳተፏ ሳይቋጭ መቋረጡ ይታወሳል፡፡
አሜሪካ እና የዓለም ባንክ በሶስቱ ሀገራት ድርድር ላይ በታዛቢነት ከመሳተፍ ባለፈ በሂደት የስምምነት ሰነድ እስከማዘጋጀት የደረሰ ተሳትፎ በማድረግ ለግብጽ ወገንተኝነታቸውን አሳይተዋል በሚል ኢትዮጵያ ቅሬታዋን አቅርባለች፡፡ የግድቡን የዉሃ ሙሌት ከሳምንታት በኋላ በክረምት ወቅት እንደምትጀምርም ኢትዮጵያ ይፋ አድርጋለች፡፡
ይሁን እንጂ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ባወጣው መግለጫ በሶስቱ ሀገራት መካከል የመጨረሻ ስምምነት ሳይደረስ የዉሃ ሙሌቱ እንዳይጀመር ማስጠንቀቁ ይታወቃል፡፡
በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲያሳድር የሚጠይቅ ደብዳቤ ግብጽ ለድርጅቱ መላኳን ተከትሎ የድርጅቱ ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሶስቱ ሀገራት አለመግባባታቸውን በ2015ቱ የካርቱም የመርሆች ስምምነት መሰረት በድርድር እንዲፈቱ ጠይቀዋል፡፡
ግብጽ የህዳሴ ግድቡ በየዓመቱ የማገኘውን የዉሃ መጠን ይቀንስብኛል የሚል ስጋት ሲኖራት ኢትዮጵያ ደግሞ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ጉልህ ጉዳት በማያደርስ መልኩ የግድቡን ግንባታና የዉሃ ሙሌት እንደምታከናውን በተደጋጋሚ መግለጿ ይታወቃል፡፡