ሂሩት በቀለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘማሪነት/አገልጋይነት ስራዎችን ስትስራ እንደነበር ይታወሳል
አንጋፋዋ ድምፃዊት ሂሩት በቀለ ባደረባት ሕመም በ83 ዓመቷ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች።
ድምጻዊት ሂሩት በቀለ በአደረባት ህመም በሃገር ውስጥና በውጭ በህክምና ስትረዳ ቆይታ በዛሬው እለት ግንቦት 04 ቀን 2015 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት መለየቷ ተነግሯል።
ሕይወት እንደሸክላን ጨምሮ በርካታ ድንቅ የሙዚቃ ስራዎችን ለአድናቂዎቿ ያደረሰችው ድምጻዊት ሂሩት በቀለ፣ ወደ ሙዚቃው ዓለም በ1949 ዓ.ም እንደገባች የሀይወት ታሪኳ ያስረዳል።
ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ጥቂት ስመጥር ሴት ድምፃዊያን መካከል አንዷ የሆነችው ሂሩት በቀለ፣ ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎቿም በሕዝብ ዘንድ እጅግ የተወደዱ እና ለበርካታ ሴት ድምፃዊያንም መነሻ የሆኑ ናቸው።
ሂሩት በቀለ በተለይ “ኢትዮጵያ” በሚል የተጫወተችው ዘፈን በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ እና ትንሽ ትልቁ በሀገር ፍቅር ስሜት የሚያዜመው ነው።
በ35 ዓመታት ውስጥ ከ200 በላይ ሙዚቃዎችን ለሕዝብ ጆሮ ያደረሰች ሲሆን ከእነዚህም መካከል ከ38 በላይ ሙዚቃዎች በሸክላ የታተሙት ናቸው። እያንዳዳቸው 10 ዘፈኖችን የሚይዙ 14 ካሴቶችንም አበርክታለች።
እስከ 1980ዎቹ መጨረሻ ድንቅ የሙዚቃ ስራዎችን ያስደመጠችን ሂሩት በቀለ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዘማሪነት/አገልጋይነት ስራዎችን ስትስራ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ሂሩት በቀለ የ7 ልጆች እናት፣የ10 ልጆች አያት እና የ7 ልጆች ቅድመ አያት ነበረች፡