አሊ መሃመድ ሙሳ (አሊ ቢራ)፤ ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ የዘለቀው የኪነጥበብ ፈርጥ
አሊ ቢራ ከኦሮምኛ በተጨማሪ አማርኛ፣ አፋርኛ፣ ሶማልኛ፣ አደሬ እና ስዊድሽ ቋንቋዎችም ይዘፍናል
በ1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ የተወለደው አሊ 267 ዘፈኖችን አለድናቂዎቹ አድርሷል
አሊ መሃመድ ሙሳ (አሊ ቢራ) በሙዚቃ ስራዎቹ ለጭቁኖች ሲታግል እንዲሁም ብዙዎችን ሲያዝናና ሲያስደስት የኖረ ነው፤ በብዙዎች ልብ ውስጥ ያረፉ ስራዎችን ለመስራት ችሎም የብዙዎችን ጆሮ ለመጎተት፤ ቀልባቸውንም ለመግዛት ችሏል።
የክብር ዶ/ር አሊ ቢራ በ1940 ዓ.ም በድሬዳዋ ከተማ ገንደ ቆሬ ሠፈር ብራ ከአባቱ አቶ መሐመድ ሙሣ እና ከእናቱ ወ/ሮ ፋጡማ አሊ እንደተወለደ የህይወት ታሪኩ ያመለክታል።
የልጅነት መጠሪያ ስሙ አሊ መሐመድ ሙሣ የሆነውና አሊ ብራ በሚል የጥበብ ስሙ የሚታወቀው እና በቅርብ ወዳጆቹ “አዴሮ (አጎት)” በሚል የፍቅርና የክብር ስምም ይጠራል።
አሊ ቢራ በ13 ዓመቱ በድምፃዊነት ሥራውን እንደ የጀመረ ሲሆን፤ በዚህም ወቅት የአፍረን ቀሎ የሙዚቃ ቡድን ማለትም ኡርጂ በከልቻ ባንድ ባዘጋጀው የበዓል ዝግጅት ላይ “ቢራዳ በሪዔ፤ ኢሊሊን ኡርጎፍቴ” የተባለ የመጀመሪያ ዘፈኑን ለህዝብ አቀረብ።
አሊ መሐመድ ሙሣም ከዚህ ሙዚቃው በኋ “አሊ ቢራ” የሚል መጠሪያ ያገኘ ሲሆን፤ በዚህም በኋላ የጥበብ ንግስና ስሙ መጠራት ጀመረ።
ሊድና ቤዝ ጊታር፣ ፒያኖ፣ ኦርጋን፣ አኮርዲዮ፣ ኡድ እና የመሳስሉት የሙዚቃ መሣሪያዎች አሊ ቢራ ከሚጫወታቸው ውስጥ ተጠቃሽ ናቸው።
አርቲስትአሊ ቢራ ከድሬደዋ ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ከታላላቆቹ የኢትዮጵያ አርቲስቶች ከእነ ጥላሁን ገሠሠ ፤መሐሙድ አህመድ፣ ብዙነሽ በቀለ እና ከመሳስሉት ጋር ለሶስት አመት አገልግሏል።
ከዚያ በኋላ በወቅቱ በነበረው አንዳንድ ተፅዕኖ በመከፋት ለዘልዓለሙ ከሙዚቃ ዓለም ለመሰናበት ወስኖ እሱን በሚያዉቁ የምድር ባቡር ኩባንያ ኃላፊዎች አማካይነት ወደ አዋሽ ከተማ ሄዶ የምድር ባቡር ጣቢያ የውሃ መካኒክ በመሆን ለማገልገል ተገደደ።
ወደ አዲስ አበባ በመመለስም በከተማዋ የመጀመሪያው የኦሮሞ ዘመናዊ የሙዚቃ ባንድ የሆነውን “አዱ ብራ ባንድ” በመመሥረት በሙኒክ ክለብ፣ በዛምቤዚክ ክለብ እና በመሳሰሉት የምሽት ከለቦች፣ ሲሠራ ቆይቷል።
በኋላም በሀገሪቱ ታላላቅ የሙዚቃ ቡድኖች ማለትም በአይቤክስ ባንድ፣ በኢትዮ ስታር ባንድና በመሳሰሉት የሙዚቃ ቡድኖች ውስጥ በዲአፍሪቅ ሆቴል፣ በራስ ሆቴል፤ በሐራምቤ ሆቴል፣ በሂልተን ሆቴል እና በመሳሰሉት ዉስጥ በድምፃዊነት ከተላላቆቹ የአገሪቱ ድምፃውያን ጋር በምሸት ከለብ በመሠራት ልዩና አቻ የሌለው የጥበብ ባለሞያነቱን ማስመርከር ንደቻል የህይወት ታኩ ያመላታል።
አሊ ቢራ ሰባት ቋንቋዎችን የሚናገር ሲሆን፤ በስድስት ቋንቋዎች ማለትም በአፋን ኦሮሞ፣ በሶማልኛ፣ በሐረሪ፣ በአማርኛ፣ በአረብኛ እና በስዊዲሽ ቋንቋዎች ዘፍኗል።
አሊ ቢራ ከዘፋኝነቱ ባሻገር የዜማ ደራሲ እና ሙዚቃ አቀናባሪ ሲሆን፤ ለጥለሁን ገሠሠ እና ለመሐሙድ አህመድ ጭምር ዜማዎችን ደርሷል።
በአጠቃለይ አሊ ቢራ በሕይወት ዘመኑ 267 ምርጥ ዘፈኖችን የዘፈነ ሲሆን፤ በዘፈኖቹም፤ ፍቅርን፣ እርቅን፣ ሰላምና መተሳስብን አጉልቶ አሳይቷል።
አሊ ቢራ የሙዚቃ ሥራው ሸልማቶችን ከአገር ዉስጥና ከውጭ አገራት ያገኘ ሲሆን፤ በአለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ያላቸው ከ100 በላይ ሸልማቶችን የወሰደ ሲሆን፤ የጅማና የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲዎችም የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አበርክተውለታል።
ከዚህም ባሻገር የጅማ ዩኒቨርሲቲ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በስሙ ሰይሟል። አዳማ ከተማ ውስጥ መንገድ፣ ድሬዳዋ ውስጥ ደግሞ ፓርክ በስሙ ተሰይሞለታል።
የክብር ዶ/ር አሊ ብራ ከፍተኛ ህመም አጋጥሞት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ጥቅምት 27 ቀን ምሽት በተወለደ በ75 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።