በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት በሀገሪቱ ያለው የአካል ጉዳተኞች ቁጥር “ሊያሻቅብ ይችላል” ተባለ
በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን ገደማ አካል ጉዳተኞች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ
በጦርነቱ በርካታ ወጣቶች ለተለያዩ የአካል ጉዳቶች መዳረጋቸውም ነው የተገለጸው
በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት በሀገሪቱ ያለው የአካል ጉዳተኞች ቁጥር “ሊያሻቅብ” እንደሚችል የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ገለጸ፡፡
የፌዴሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አባይነህ ጉጆ ለአል-ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት ከሆነ፤ ጦርነቱ በርካቶችን በተለይም አምራች ኃይል የሆነውን ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል የጎዳ ነው፡፡
“በጦርነቱ በርካታ ወጣቶች እጅና እግራቸው እንዲሁም አይንና ጆሯቸውን ያጡበት ሁኔታ አለ”ም ነው ዋና ዳይሬክተሩ ያሉት፡፡
አካል ጉዳተኝነት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ሊያጋጥም የሚችል ነው የሚሉም ሲሆን ሰው ሰራሹ ጦርነት የሰዎችን አካል ሊያጎድሉ ከሚችሉ መንስኤዎች አንዱ ነው፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም አሁን ባለው ሁኔታ ያልተመጣጠነ የምግብ ስርአት እና ያልተመቸ የትራንስፖርት አገልግሎት አካል ጉዳተኝነትን ሊያስከትሉ ከሚችሉ መንስኤዎች መካከል ናቸው ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አካል ጉዳተኞች አሉ እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ፡፡ በመሆኑም የአካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች መሰራት አለባቸው፡፡
አቶ አባይነህ፤ እሳቸው በሚመሩት ፌዴሬሽን እና በመንግስት በኩል አካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ያደረጉ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንና ያነሱ ሲሆን ፤ ሁሉም የህብረተስብ ክፍሎች ከመንግስት ጋር በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ 20 ሚሊዮን ገደማ አካል ጉዳተኞች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ቁጥሩ በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት የተጎዱ ኢትዮጵያውያንን አያካትትም፡፡ ይህም በሃገሪቱ የሚኖረው የአካል ጉዳተኞች ቁጥር እንደሚሻቅብ አመላካች ነው፡፡
ቁጥሩ ምናልባትም ከአንዳንድ የአውሮፓ እና አፍሪካ ሀገራት አጠቃላይ የህዝብ ብዛት የሚበልጥ አካል ጉዳተኛ በኢትዮጵያ ለመኖሩ አመላካች ነው እንደ አቶ አባይነህ ገለጻ፡፡
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን 25ኛ ዓመት የምስረታ ቀን በአዲስአ አበባ ተከብሯል፡፡