ከ60 ዓመታት በኋላ የተሻሻለው አዲሱ የንግድ ህግ ምን ያህል እየተፈጸመ ነው?
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር የተሻሻለው የንግድ ተግባረዊነቱ ዘግይቷል ብላል
የንግድ ህጉ አንድ ግለሰብ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማቋቋምን ቢፈቅድም እስላሁን ተግባራዊ አልሆነም
ኢትዮጵያ በ2013 ዓ.ም ላለፉት ስድስት አስርት ዓመታት የተገዛችበትን የንግድ ህግ አሻሽላለች።
በ1952 ዓ.ም. የወጣውና አምስት ጥራዞችን የያዘው ህግ ሀገሪቱ ከደረሰችበት የንግድ እንቅስቃሴ ጋር አይጣጣምም የሚል ትችት ሲቀርብበት ነበር። በመሆኑም የዓለምንም ሆነ የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት በሚል ላለፉት ሁለት አስርት ዓመታት ገደማ ተጠንቷል።
በአዲሱ የንግድ ህግ ሁለት ጥራዞች ወጥተው፤ አዳዲስ የንግድ አይነቶችን ተጨምረው፤ የተለያዩ ክፍሎች ደግሞ ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል።
ከእነዚህ ማሻሻያዎች አንዱ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማቋቋምን ይመለከታል። በቀደመው ህግ ይህን ማህበር ለማቋቋም ሁለትና ከዚህ በላይ የሆኑ ግለሰቦች ብቻ ይፈቀድ ነበረ ሲሆን፤ ይህም ለህጉ ሲባል በተለይም የውጭ ባለሀብቶችን ለወጪ መዳረጉ ይነሳል።
አዲሱ ህግ አንድ ግለሰብ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ማቋቋምን ፈቅዷል። ሆኖም እስካሁን ገቢራዊ እየሆነ አይደለም። ለምን ሲል አል ዐይን አማርኛ የጠየቀው የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር ህጉን ስርዓት የሚያሲዘው መመሪያ ባለመውጣቱ ነው ብሏል።
የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚንስቴር የፈቃድና ቁጥጥር ስራ አስፈጻሚ ጅራታ ነመራ መመሪያው አሁን ላይ ጸድቆ በፍትህ ሚንስቴር ተመዝግቧል ብለዋል።
“ስራ ላይ የነበረው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ማሻሻያዎች ከተደረጉ በኋላ መመሪያ ማሻሻል ያስፈልግ ነበር። መመሪያውን አሻሽለን [በታህሳስ ወር] ጨርሰናል። ጸድቆም ወጥቷል። የንግድ ምዝገባ፣ ፈቃድ እና ድህረ ፈቃድ ኢንስፔክሽን መመሪያ 935/2015 በሚል በፍትህ ሚንስተር ተመዝግቧል” ብለዋል።
መመሪያው አጠቃላይ የንግድ ህጉ ላይ ያሉትንና ሌሎች ተዛማጅ ክፍሎች ላይ ያሉ ጉዳዮችን ወደ ንግድ ፈቃድ አሰጣጥ ስርዓት በማካተት መሟላት ያለባቸው መስፈርቶችን እንደሚያካትትም ተናግረዋል።
የንግድ ህጉን መሠረት አድርጎ ወጥቷል የተባለው መመሪያ፤ ወጥነት ኖሮት ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ ተያያዥ የሆነ የንግድ ስርዓት እንዲኖር ተሰራጭቷል ነው የተባለው።
ባለ አንድ አባል ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ድረ-ገጽ በልጽጎ በዚህ ዓመት አገልግሎት መስጠት በጀመረው የኦንላይን ስርዓት እየተተገበረ አለመሆኑን አል ዐይን አረጋግጧል።
ጅራታ ነመራ አልሚ ድርጅቱ በስርዓቱ ላይ ማሻሻያውን ጭማሪ እንዳያደርግ መሰጠቱን ተናግረዋል።ሆኖም ታህሳስ ወር የንግድ ቢሮዎች ንግድ ፍቃድ ማደስ ተደራራቢ ስራ ስለገጠማቸው መጀመር አልተቻለም ብለዋል።
“መስፈርቶቹ ተዘጋጅተው እንዲገቡ ተደርጓል። የምስክር ወረቀት (ሰርተፍኬት) ዲዛይን ብቻን ነበር የሚቀረው” ብለዋል።
ኃላፊው አገልግሎቱን ስራው ቶሎ አልቆ መስጠት እንደሚጀምሩ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል፤ በዚህ ቀን ብለው ቀን ባይቆርጡ።